የኦነግ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ባልታወቁ ሰዎች በጥይት ተመትቶ ሕይወቱ አለፈ

Moibon Bekele

የፎቶው ባለመብት, Moibon Bekele FB

ታትሟል

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የሆነው አቶ ሞኢቦን በቀለ ማንነታቸው ባልታወቀ ሰዎች ከአዲስ አበባ ዳርቻ በምትገኘው ቡራዩ ውስጥ በጥይት ከተመታ በኋላ ሕይወቱ አለፈ።

አቶ ሞኢቦን ጥቃቱ የተፈጸመበት ረቡዕ ጥቅምት 02/2015 ዓ.ም. ቡራዩ ሳንሱሲ ተብሎ በሚጠራው የመኖሪያ አካባቢው አመሻሽ ላይ ነው።

የኦነግ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የሆነው ግለሰቡ ጥቃቱን በፈጸሙበት ሰዎች በሁለት ጥይት ከተመታ በኋላ ሕይወቱ ያለፈው ወደ ለሕክምና እርዳታ ሆስፒታል ከደረሰ በኋላ ነው።

የሕክምና ድጋፍ ሲደረግለነት ከነበረው አቤት ሆስፒታል ምንጮች የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ሞኢቦን፤ ቢያንስ በሁለት ጥይት ተመትቷል።

የመጀመሪያው ጥይት በሳምባው አካባቢ አልፎ የወጣ ሲሆን፤ ሁለተኛው እና ከፍተኛ ጉዳት አድርሶበታል የተባለው ጥይት ኩላሊቱ አካባቢ እንደቀረ ተገልጿል።

ረቡዕ ምሽት 1 ሰዓት አካባቢ በጥይት ጥቃቱ ከተፈጸመበት በኋላ ወደ ሆስፒታል የተወሰደው አቶ ሞኢቦን፣ በደረሰበት ጉዳት የሕክምና እርዳታ እየተደረገለት ሳለ የዚያኑ ዕለት ምሽት 5 ሰዓት ገደማ ሕይወቱ ማለፉን ቤተሰቦቹ ተናግረዋል።

ቢቢሲ ከቤተሰቡ እንደተረዳው ከሆነ፤ ጥቃቱ በተፈጸመበት ምሽት ሞኢቦን በመኖሪያ ቤቱ ምግብ እየተመገበ ሳለ ስልክ ተደውሎለት በፍጥነት ከወጣ በኋላ ነው በጥይት የተመታው።

ሞኢቦን በጥይት ከተመታ በኋላ እርዳታ ለማግኘት ለቅርብ የቤተሰብ አባሉ ስልክ መደወሉን እና ይህን ጥቃት ሊያደርስበት የሚችል “ጠላት የለኝም፤ የምጠረጥረውም የለም” ሲል መናገሩን አንድ የቤተሰብ አባል ገልጿል።

ሞኢቦን የኦነግ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ከመሆኑ በተጨማሪ ሕይወቱ እስካለፈበት ዕለት ድረስ የኢትዮ-ቴሌኮም ባልደረባ ሆኖ ሲሰራ ነበር።

የኦነግ ቃል አቀባይ ለሚ ገመቹ ለቢቢሲ ሲናገሩ ሞኢቦን ባለፉት አምስት ዓመታት የፓርቲው የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ሆኖ ሲሰራ መቆየቱን ተናግረው፤ በፖለቲካዊ ምክንያቶች በተደጋጋሚ ለእስር ሲዳረግ መቆየቱን ተናግረዋል።

የሞኢቦን የረዥም ዓመታት ወዳጅ እንደሆነ የሚናገረው ላሊሳ ኢድሪስ በተመሳሳይ ሟቹ በፖለቲካ አቋሙ በተደጋጋሚ ሲታስር መቆየቱን እና ከጅም ዩኒቨርሲቲም ተባሮ እንደነበረ አስታውሷል።

“ሞኢቦን በፖለቲካ ምክንያት ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ከተባረረ በኋላ ወደ ነቀምቴ ተመልሶ በሪፍትቫሊ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ሲከታተል ከዚያም ተይዞ በቂሊንጦ ታስሮ ነበር።”

ጓደኛው እንደሚለው ሞኢቦን ከዚህ ቀደም ጅማ ከተማ ባለ እስር ቤት፣ በማዕከላዊ፣ ቂሊንጦ እና ሸዋ ሮቢት ማረሚያ ቤቶች ታስሮ ነበር።

"ግድያዎች አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሰዋል"

ወጣቱ የኦነግ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል በቀለ በጥይት ተመትቶ ሕይወቱ ማለፉ ከተሰማ በኋላ ፓርቲው መግለጫ አውጥቷል።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር በመግለጫው "በአገሪቱ በሰዎች ላይ የሚፈጸመው ግድያ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል" ብሏል።

ወጣት እና ቆራጥ የሆነ አባልና የፖለቲካ አመራር በማጣቱ ከፍተኛ ሐዘን እንደተሰማው የገለጸው ፓርቲው፤ "የፓርቲው አባላት እና ኦሮሞዎች የሚከፍሉት መስዋዕትነት የሚደረገውን ትግል እንደማያስቆም እና ተሰፋ እንደማያስቆርጥ" ገልጿል።

የሞኢቦን በቀለ አስክሬን ከአዲስ አበባ ወደ ነቀምት የተወሰደ ሲሆን፣ የቀብር ሥነ ሥርዓቱም ዛሬ አርብ ጥቅምት 04/2015 ዓ.ም. እንደሚፈጸመው ቤተሰቦቹ ተናግረዋል።