መርማሪ ቡድኑ በትራምፕ ላይ መጥሪያ እንዲቆረጥባቸው ወሰነ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ባለፈው ዓመት የአሜሪካ ምርጫን ተከትሎ የተነሳውን ነውጥ ለመመርመር በሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባላት የተዋቀረውና 9 አባላት ያሉት መርማሪ ኮሚሽን ትናንት ምሽት ምርመራውን አጠናቋል።
በዚህ የመጨረሻ ነው በተባለ የምርመራ ውጤት የመርማሪ ኮሚሽኑ አባላት በትራምፕ ላይ መጥሪያ እንዲቆረጥና ስለሆነው ነገር ሁሉ ቃል እንዲሰጡ በሙሉ ድምጽ ወስነዋል።
‘ለፈጸመው ተግባር ምላሽ እንዲሰጥ ግድ ይላል’ ብለዋል የሚሲሲፒው ዲሞክራት ወኪልና የመርማሪ ሸንጎው ሊቀ መንበር የሆኑት ቤኒ ቶምሰን።
ትራምፕ መጥሪያውን ቸል ካሉ ክስና እስር ይጠብቃቸዋል።
ይህ መርማሪ ሸንጎ የትራምፕ ነውጠኛ ደጋፊዎች ካፒቶል ሒልን ሰብረው ያደረሱትን ጥፋት ሲመረምር ድፍን ዓመት አልፎታል።
በዚህ ሸንጎ ከ 9 አባላት ሁለቱ ሪፐብሊካን፣ 7ቱ ደግሞ ዲሞክራቶች ናቸው።
የመርማሪ ኮሚሽኑ አባላት ትራምፕ መጥሪያ ተቆርጦላቸው ቃላቸውን እንዲሰጡ የወሰኑት ያለምንም ተቃውሞና ድምጸ ተአቅቦ በሙሉ ድምጽ ነው።
ለትራምፕ መጥሪያ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ተቆርጦ ይሰጣቸዋል።
የዋዮሚንግ ግዛትና የሪፐብሊካን ተወካይ እንዲሁም የመርማሪው ሸንጎ ምክትል የሆኑት ሊዝ ቼኒ እንዳሉት አሜሪካዊያን ለዚሁ ሁሉ ጥፋት መሠረት ነው ከሚባለው ሰው ሐቁን የመስማት መብት አላቸው።
ትናንት በኢትዮጵያ አቆጣጠር ማታ 2፡00 ሰዓት የጀመረው የመርማሪ ቡድኑ 9ኛ ሸንጎ የመጨረሻ ምርመራ ሰነዶችና የቪዲዮ ማስረጃዎች የቀረቡበት ነበር።
በርካታ አስደንጋጭ የተባሉ መረጃዎችም ለሕዝብ በቀጥታ ቴሌቪዥን እንዲታዩ ሆነዋል።
በዚህ የቪዲዮ ማስረጃ በተለይካፒቶል ሒል ውስጥ የነበሩ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባላት፣ አፈ ጉባኤ ናንሲ ፒሎሲን ጨምሮ ከቢሮ ቢሮ ሲሯሯጡ፣ ለዶናልድ ትራምፕ የቅርብ ሰዎች ስልክ ሲደውሉና በከፍተኛ ጭንቅ ከነውጠኞቹ ለማምለጥ ሲሞክሩ የሚያሳዩ አዳዲስ ቪዲዮዎች ለሕዝብይፋ ተደርገዋል።
እንደራሴዎቹ በተለይ የጋዝ መከላከያ ጭንብል ሲለብሱና በነፍስ ግቢ ነፍስ ውጪ ሁኔታ ሆነው ሲንቀሳቀሱ የቪዲዮ ማስረጃዎች የቀረቡበት ነበር የትናንቱምስክርነት።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዶናልድ ትራምፕ ይህን የመርማሪ ኮሚሽኑን ውሳኔ ፖለቲካዊ ብለውታል።
‘አሜሪካዊያን በዲሞክራቶች ቀሽም አመራር በተማረሩበት ወቅት የፖለቲካ ነጥብ ለማስቆጠር የተቀናበረ ነው፤ የእኔን ምስክርነትከፈለጉ ለምን በምርመራው መጀመርያ አልጠየቁኝም?’ ብለዋል ትራምፕ።
ዶናልድ ትራምፕ በ2024 በድጋሚ ለፕሬዝዳንትነት ለመወዳደር ፍላጎት እንዳላቸው ፍንጭ ሰጥተዋል።
አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች ይህ የምርመራ ቡድኑ ውሳኔ ከወር በኋላ ከሳምንታት በኋላ የሚደረገው ‘ሚድተርም’ ምርጫ ላይ ዲሞክራቶች ሊደርስባቸው የሚችለውን ሽንፈት በመስጋት መራጮችን ለማማለል ሆን ተብሎ የተደረገ ነው ይላሉ።
ይህ በሕዝብ እንደራሴዎች የተቋቋመው መርማሪ ቡድን ሙሉ የምርመራ ውጤቱን ከሁለት ወራት በኋላ ይፋ ያደርጋል።
ለዓመት ያህል በዘለቀው ምርመራ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣናትን፣ የደህንነት ሰዎችን፣ ሚኒስትሮችን፣ የዶናልድ ትራምፕ የቀድሞ ረዳቶችን፣ የጸጥታ አካላትን ጨምሮ ከአንድ ሺህ አሜሪካዊያን በላይ ምስክርነት ሰምቶ መርምሯል።
በዚህ መርማሪ ቡድን ሁለቱ ብቸኛ የሪፐብሊካን ፓርቲ አባል የሆኑት ሊዝ ቼኒ እና አዳም ኪዚንግር ትናንት ትራምፕ የምስክርነት ማዘዣ ተቆርጦባቸው ቃላቸውን እንዲሰጡ ድምጽ በመስጠታቸው በፓርቲያቸው ዘንድ ከፍተኛ ውግዘት ደርሶባቸዋል።
በባለፈው ዓመት የትራምፕ ነውጠኛ ደጋፊዎች የካፒቶል ሒል አመጽ 850 አሜሪካዊያን ክስ ተመስርቶባቸዋል።












