ተዋናዩ አሌክ ባልድዊን በቸልተኝነት የሰው ሕይወት በማጥፋት ክስ ሊመሰረትበት ነው

አሌክ ባልድዊን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ታዋቂው የፊልም ተዋናይ አሌክ ባልድዊን ሲኒማቶግራፈር ሀሊና ሀቺንስን የፊልም ቀረጻ ላይ እያሉ ተኩሶ በመግደሉ፣ በቸልተኝነት የሰው ሕይወት በማጥፋት ክስ ሊመሰረትበት ነው።

ግድያው በተፈጸመበት ወቅት ባልድዊን ‘ረስት’ ለተሰኘው ፊልም ቀረጻ ልምምድ ላይ ነበር ተብሏል።

አደጋው የተፈጠረው ሳንቴ ፌ በተሰኘችው በኒው ሜክሲኮ ግዛት በምትገኝ ከተማ በአውሮፓውያኑ 2021 ጥቅምት ወር ላይ ነበር።

ተዋናዩ ባለማወቅ ተቀባብሎ በተዘጋጀ ሽጉጥ በተኮሰው ጥይት የ42 ዓመቷን የፎቶግራፍ ዳይሬክተሯን በጥይት ሲገድል፤ ዳይሬክተሩን ደግሞ አቁስሏል።

ከአሌክ ባልድዊን ጋርም በፊልሙ ቀረጻ ላይ የመሳሪያ ተቆጣጣሪ ሆና ትሰራ የነበረችው ሐና ጉቴሬዝ ትከሰሳለች ተብሏል።

የሁለቱም ጠበቆች ጉዳዮን በችሎት ፊት ለመከራከር መወሰናቸውን ተናግረዋል።

የሳንታ ፌ ዐቃቤ ሕግ የሆኑት ማሪ ካርማክ አልትዌይስ የክሱን ይዘት ሐሙስ ዕለት ያሳወቁ ሲሆን፣ በዚህ ወር መጨረሻ ላይ ክስ እንደሚመሰርት ገልጸዋል።

“ተዋናይ እና ፕሮዲውሰር አሌክ ባልድዊን እንዲሁም የፊልሙ የመሳሪያ ተቆጣጣሪ የሆነችው ሐና ጉቴሬዝ ሪድ በቸልተኝነት የሰው ሕይወት በማጥፋት ክስ ይመሰረትባቸዋል. . . ለዚህ የሚሆን በቂ ማስረጃ አለን ብዬ አምናለሁ” ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

“እኔ እዚህ ቦታ ላይ እስካለሁ ድረስ ማንም ሰው ከሕግ በላይ አይሆንም፤ እናም ሁሉም ሰው ፍትህ ያስፈልገዋል” ሲሉ አክለዋል።

ሁለቱም ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ የ18 ወራት እስር እና የ5ሺህ የአሜሪካ ዶላር ቅጣት ይጠብቃቸዋል።

የፊልሙ ዳይሬክተር ጆዬል ሶውዛ ጉዳት የደረሰበት ቢሆንም፣ እርሱን በሚመለከት ግን የሚመሰተረት ምንም ዓይነት ክስ የለም ተብሏል።

የፊልሙ ረዳት ዳይሬክተር ዴቪድ ሀልስ አደገኛ መሳርያን በቸልተኝነት በመጠቀም ለቀረበበት ክስ ጥፋተኛ መሆኑን አምኖ የክስ ማቅለያ ማስገባቱን ዐቃቤ ሕጓ ተናግረዋል።

ለዚህም ከማረሚያ ቤት ውጪ ሆኖ ስድስት ወር በፖሊስ ክትትል ውስጥ እንዲቆይ ተወስኖበታል።

ይህ የዐቃቤ ሕጓ ውሳኔ ከተሰማ በኋላ የሀቺንስ ባለቤት፣ ማቲው በጠበቃው በኩል ባወጣው መግለጫ ላይ የክሱን መመስረት እንደሚደግፍ አስታውቋል።

“በኒው ሜክሲኮ ማንም ሰው ከሕግ በላይ አለመሆኑን ማወቅ ለቤተሰቡ የአእምሮ እረፍት ነው።”

ነገር ግን የባልድዊን ጠበቃ ሉክ ኒካስ ውሳኔውን በመቃወም “አሳፋሪ የሆነ የፍትህ ጭንገፋ ነው” ሲል አጣጥሎታል።

“ባልድዊን በሽጉጡ ውስጥ ጥይት ተቀባብሎ ስለመቀመጡ ምንም እውቀት አልነበረውም” ካለ በኋላ “አብሯቸው በሚሰራቸው ሰዎችን ሙያዊ ሥነ ምግባር ተማምኖ ሽጉጡ ተተኳሽ ጥይት እንደሌለው የነገሩትን አምኖ ተቀብሎ ነበር፤ ይህንንም አቅርበን እንከራከራለን፤ ደግሞም እናሸንፋለን።”

የጉቴሬዝ ሪድ ጠበቃ በበኩላቸው የዐቃቤ ሕጓ ውሳኔ “የተዛባ ምርመራ ውጤት እና አጠቃላይ ስለተከሰተው ሁኔታ የተሳሳተ መረዳት መኖሩን ያሳያል” ብለዋል።

አክለውም ሐና ስለተፈጠረው ሁኔታ ሁሌም ታዝናለች ካሉ በኋለ “በቸልተኝነት ግን የሰው ሕይወት አላጠፋችም” ሲሉ ከወዲሁ አስተባብለዋል።