ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የዩናይትዱ ሜሰን ግሪንውድ ቀርቦበት የነበረው የአስገድዶ መድፈር ክስ ውድቅ ተደረገ
በማንችስተር ዩናይትድ ተጫዋቹ ሜሰን ግሪንውድ ላይ ቀርቦበት የነበረው የአስገድዶ መድፈር እና የጾታዊ ጥቃት ክስ ውድቅ ተደረገ።
የ21 ዓመቱ እግር ኳስ ተጫዋች የሴት ጓደኛው ላይ ያደረሰውን ጉዳት ያሳያሉ የተባሉ ፎቶግራፎች እና ተንቀሳቃሽ ምስሎች ማሕበራዊ ሚዲያዎች ላይ በስፋት መሰራጨታቸውን ተከትሎ ከአንድ ዓመት በፊት በቁጥጥር ሥር ውሎ ነበር።
ከዚያም በአስገድዶ መድፈር፣ በአደገኛ ባህሪ እና በአካል ላይ ጉዳት በማድረስ ክስ ቀርቦበት ነበር።
ክሱ ውድቅ መሆኑ ከተሰማ በኋላ ግሪንውድ ውሳኔው ‘እረፍት እንደሰጠው’ ገልጾ ለተሰጠው ድጋፍ ቤተሰቡን እና ጓደኞቹን አመስግኗል።
በግሪንውድ ስም የወጣው መግለጫ ተጫዋቹ በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ አስተያየት እንደማይሰጥ አመልክቷል።
ዐቃቤ ሕግ ክሱ ውድቅ የሆነው በክስ ሂደቱ ቁልፍ የነበሩት የዓይን እማኞች ተሳትፏቸውን ካቆሙ በኋላ ነው ብሏል።
የዐቃቤ ሕግ ቃል አቀባይ የዓይን እማኝ ተሳትፎ መቆም እና አዲስ ማስረጃ መገኘቱ ክሱ ፍርድ የማስከተል ዕድሉ አነስተኛ ነው ብለዋል።
“ውሳኔያችንን ለሁሉም አካላት አሳውቀናል። ጉዳት የደረሰበት ማንኛወም ሰው ወደፊት መጥቶ ሪፖርት እንዲያደርግ እናበረታታለን” ብለዋል ቃል አቀባዩ።
ግሪንውድ በአንዲት ሴት ላይ ድብደባ ፈጽሟል የሚሉ ክሶች መሰማታቸውን ተከትሎ ክለቡ ማንችስተር ዩናይትድ ከልምምድ አግዶት ቆይቷል።
ክለቡ በግሪንውድ ላይ ቀርቦ የነበረው ክስ እንዲቋረጥ መደረጉን እንደተገነዘበ ገልጾ ቀጣይ እርምጃዎች ላይ ከውሳኔ ከመድረሱ በፊት የራሱን የውስጥ ምርመራ እንደሚያደርግ አስታውቋል።
“ይህ ምርመራ እስከሚጠናቀቅ ድረስ በጉዳዩ ላይ አስተያየት አንሰጠም” ብሏል ማንችስተር ዩናይትድ።
ማንችስተር ዩናይትድ የሚያደርገው ምርመራ እስኪጠናቀቅ ድረስ ግሪንውድ ልምምድም ሆነ በጨዋታ ተሰልፎ እንደማይጫወት ቢቢሲ ከምንጮቹ ተረድቷል።