ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ባይደን መጪውን ምርጫ አሸንፋለሁ ሲሉ ለግንዘብ ለጋሾቻቸው ማረጋገጫ ሰጡ
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከደካማ የምርጫ ክርክራቸው በኋላ በዕጩነታቸው ዙሪያ ብዙ ጥያቄዎች መነሳታቸውን ተከትሎ ከዶናልድ ትራምፕ ጋር የሚያደርጉትን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንደሚያሸንፉ ለዴሞክራት ፓርቲ የገንዘብ ለጋሾች ማረጋገጫ ሰጡ።
የ81 ዓመቱ ፕሬዝዳንት ቅዳሜ ዕለት በኒው ዮርክ እና በኒው ጀርሲ በተደረጉ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅቶች ላይ ተገኝተው በሲኤንኤን ፕሬዝዳንታዊ የምርጫ ክርክር ላይ ያሳዩትን አቋም ተከላክለዋል።
ከዝግጅቶቹ በአንዱ ላይ ሲናገሩ “በጣም ጥሩ አልነበርኩም። ትራምፕም ጥሩ አልነበረም“ ብለዋል ባይደን።
"በዚህ ምርጫ እንደምናሸንፍ ቃል እገባላችኋለሁ" ሲሉ አክለዋል።
ፕሬዝዳንቱ በሑሙሱ የምርጫ ክርክር ባሳዩት አቋም ዙሪያ ያለውን ስጋት እንደተረዱ እና የበለጠ ለመሥራት ቃል ገብተዋል።
ዴሞክራቱ የኒው ጀርሲ አገረ ገዥ ፊል መርፊ ከፕሬዝዳንት ባይደን እና ከቀዳማዊት እመቤት ጋር በመሆን በገቢ ማሰባሰቢያው ላይ ተገኝተው “ሁላችንም ከእርስዎ ጎን ነን” ሲሉ ለፕሬዝዳንቱ ድጋፋቸውን ገልጸዋል።
ባይደን ከቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ባካሄዱት የምርጫ ክርክር ባሳዩት አቋም ክርክሩን ለመከታተል አስቸጋሪ እና ግራ አጋቢ በሆኑ መልሶች የተሞላ ነበር። ይህን ተክትሎም ፕሬዝዳንቱ በዚህ ምርጫ ለመወዳደር ትክክለኛው እጩ ስለመሆን በአንዳንድ ዴሞክራቶች ዘንድ አዲስ ጥያቄዎችን አስነስቷል።
የቀድሞ የምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ናንሲ ፔሎሲ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከሆነ የባይደን የምርጫ ክርክር አፈጻጸም “በጣም ጥሩ አልነበረም።” የቀድሞ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ኬት ቤዲንግፊልድ በበኩላቸው “በእውነት ተስፋ አስቆራጭ” ብለውታል።
የባይደን የቅርብ ጓደኛ የሆኑት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ በማህበራዊ ሚዲያ "መጥፎ የምርጫ ክርክር ምሽት ነበር” ብለዋል።
"አሁንም ቢሆን ይህ ምርጫ ህይወቱን ሙሉ ለተራ ዜጋ በታገለ እና ለራሱ ብቻ በሚያስብ መካከል የሚደረግ ነው" ሲሉ ኦባማ ጽፈዋል።
ከክርክሩ ከሰዓታት በኋላ ትራምፕ የምርጫ ክርክሩን ለምርጫ ዘመቻቸው "እንደ ትልቅ ድል" አድርገው እንደሚቆጥሩት ለደጋፊዎቻቸው ከመናገር ባለፈ ባይደንን "በፍፁም ብቃት የሌላቸው” ሲሉ ገልጸዋቸዋል።
"የጆ ባይደን ችግር የዕድሜው ጉዳይ አይደለም" ብለዋል የ78 አመቱ ትራምፕ።
የባይደን አፈጻጸም የተተቸው በፖለቲካ ውስጥ ባሉ ሰዎች ብቻ አይደለም።
በኒው ዮርክ ታይምስ ላይ ታዋቂ የሆነው ርዕሰ አንቀጽ ባይደን በድጋሚ ለመወዳደር መወሰናቸውን “በግድ የለሽነት የተሞላ ቁማር" ሲል ገልጾታል።
ዴሞክራቶች “ባይደን ውድድሩን መቀጠል እንደማይችሉ አምነው መቀበል እና በእሳቸው ቦታ መወዳደር የሚችል ሰው ለመምረጥ መዘጋጀት አለባቸው” ብሏል።
የሐሙሱን የምርጫ ክርክር ተከትሎ በመላው ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ መራጮች ለሁለቱም ዕጩዎች ድምጽ ለመስጠት ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል።
ለረዥም ጊዜ ዴሞክራት ፓርቲ አባል የሆኑት ሎሪ ግሪጎሪ ክርክሩን ለመመልከት “አቅም እንዳጡ” ለቢቢሲ ተናግረው “አገራችን ልታቀርባቸው የምትችላቸው ዕጩዎች እኚሁ ናቸው?" ሲሉ ጠይቀዋል።
ሪፐብሊካኗ ክሪስታል ማየርስ-ባርበር በበኩላቸው ፉክክሩን “ማየት በጣም ያሳምማል" ሲሉ ተናግረዋል።
ከክርክሩ በኋላ በዳታ ፎር ፕሮግረስ የተደረገ የሕዝብ አስተያየት እንደሚያሳየው ክርክሩን ከተመለከቱ ወይም ስለ ክርክሩ ካነበቡ መራጮች መካከል 62 በመቶ የሚሆኑት ትራምፕ አሸንፈዋል ብለዋል። አስተያየት ከተሰጡት ውስጥ 30 በመቶዎቹ ባይደን በክርክሩ አሸንፈዋል ብለዋል።