አሜሪካዊቷ ዳኛ የክሪስቲያኖ ሮናልዶን የክስ መዝገብ ውድቅ አደረጉ

ታትሟል

አሜሪካዊቷ ዳኛ የክሪስቲያኖ ሮናልዶን የመድፈር ወንጀል መዝገብ በቂ ማስረጃ አልቀረበበትም በማለት ውድቅ አድርገውታል።

ዳኛዋ፤ የከሳሽ ጠበቃ የተሰረቁና ሾልከው የወጡ መረጃዎች ብቻ ናቸው ያሏቸው ብለዋል።

ካትሪን ማዮርጋ በፈረንጆቹ 2009 ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ላስ ቬጋስ ያለ ሆቴል ውስጥ ደፍሮኛል ስትል ትከሳለች።

በዚህ ክስ ተፈርዶበት የማያውቀው እግር ኳስ ተጫዋቹ ክሱን አይቀበለውም።

በ2010 ከፍርድ ቤት ውጭ ክሱን ለማቋረጥ 375 ሺህ ዶላር ተቀብላለች የሚሉ ዘገባዎች ወጥተው ነበር።

ማዮርጋ እንደምትለው ምንም እንኳ ገንዘቡን ለመቀበል ብትስማማም በወቅቱ ባደረባት የአእምሮ መረበሽ በሂደቱ ላይ ልትሳተፍ አልቻለችም።

አክላ ገንዘቡን እንድትቀበል ከፍተኛ ተፅዕኖ ያርፍባት እንደነበር ትናገራለች።

አሜሪካዊቷ ዳኛ ጄኔፌር ዶርዚ የከሳሿ ጠበቃ የክስ መዝገቡን የከፈቱት በተገቢው መንገድ ያልተገኙ ማስረጃዎችን አጠረቃቅመው ነው ብለዋል።

ዳኛዋ አክለው የከሳሿ ጠበቃ በተሰረቁና ባልሆነ መንገድ በተገኙ ማስረጃዎች ተከሳሹን አደጋ ላይ ጥለዋል ብለዋል።

42 ገፅ ባለው ክሱን መሻሩን በሚገልጠው ደብዳቤ ዳኛ የከሳሽ ጠበቃ ሌዝሊ ስቶቫል "የክስ ሂደቱን ባልሆነ መንገድ በመምራት ከሳሿ ተገቢውን ፍርድ እንዳታገኝ አድርገዋል" ሲሉ ወቅሰዋል።

ባለፈው ዓመት አንድ ሌላ ዳኛ ጠበቃው ሥነ-ሥርዓት የላቸውም በማለት መዝገቡ ውድቅ እንዲሆን ጠይቀው ነበር።

ቢቢሲ ጠበቃውን ለማናገር ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።

በ2019 የአሜሪካ አቃቤያነ ሕግ "ክሱ በቂ ማስረጃ ሊቀርብበት ስላልቻለ" ክሪስቲያኖ ሮናልዶ አይከሰስም ብለው ነበር።

ማዮርጋ ምንም እንኳ ተጫዋቹ ደፈረኝ ብትልም መቼና የት እንዲሁም ጥቃት የፈፀመው ማን እንደሆነ ልትናገር ፈቃደኛ አይደለችም ይላል የላስ ቬጋስ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ቢሮ።

ነገር ግን በከሳሿ ጥያቄ መሠረት ክሱ በ2018 እንደ አዲስ ምርመራ እንዲደረግበት ተደርጓል።

የጀርመኑ ጋዜጣ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ለማዮርጋ ከፍርድ ቤት ውጭ ገንዘብ ለመክፈል ተስማምቷል ሲል ያስነበበው በ2107 ነበር።

የማዮርጋ ጠበቃ ከሳሿ መዝገቡ እንደ አዲስ እንዲከፈት የወሰነችው #MeToo በተሰኘው ንቅናቄ ተነሳስታ ነው ይላሉ።

ሮናልዶ በ2009 ላስ ቬጋስ ውስጥ ከማዮርጋ ጋር እንደተገናኘ አይክድም።

ነገር ግን በሁለቱ መካከል የተፈጠረው ነገር የሆነው በፈቃደኝነት እንደሆነ ይናገራል።