ዶክተር ሊያ ታደሰን ተክተው የጤና ሚኒስትር የሆኑት ዶክተር መቅደስ ዳባ ማን ናቸው?

ታትሟል

ዶክተር መቅደስ ዳባ፣ የቀድሞ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰን እንዲተኩ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተሾሙ።

ዛሬው ጥር 30/2016 ዓ.ም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረገው መደበኛ ስብሰባው ጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አህመድ የስራ ልምዳቸውን ካቀረቡ በኋላ ዶክተር መቅደስ ዳባ የጤና ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል።

አዲሷ የጤና ሚኒስትር በዓለም ጤና ድርጅት ዋና መስሪያ ቤት ጄኔቫ የተቋሙ ምክትል ዳይሬክተር ልዩ ረዳት እና ከፍተኛ ባለሙያ ሆነው በማገልገልም ላይ ነበሩ።

ዶክተር መቅደስ ከመጋቢት 03 2012 ዓ.ም ጀምሮ ለአራት ዓመታት ገደማ በስልጣን ላይ የነበሩትን ዶክተር ሊያ ተሾመን ይተካሉ።

ዶክተር ሊያ በተለይም የኮቪድ- 19 ወረርሽኝ በኢትዮጵያ በተስፋፋበት ወቅት በኃላፊነት የመሩ ሲሆን ሲሆን ከዚያ ቀደም ብሎ ደግሞ በዚሁ ሚኒስቴር መስሪያቤት በሚኒስትር ዲኤታነት ሰርተዋል።

የቀድሞ የጤና ሚኒስትሯ፣ ለምን እንደተተኩ በሳቸውም ይሆን በመንግሥት በኩል የተባለ ነገር የለም።

ዶክተር መቅደስ ዳባ ማን ናቸው?

አዲስ አበባ የተወለዱት የጽንስ እና ማህጸን ሐኪሟ ዶክተር መቅደስ ዳባ ፈይሳ ባለፈው ዓመት መግቢያ ላይ በህክምና ዘርፍ ላይ ባደረጉት ምርም እና አስተዋጽኦ በሴቶች ዘርፍ የዓለም የፅንስና ማህፀን ህክምና ሽልማትን አሸናፊ ሆነዋል።

ተባባሪ ፕሮፌሰሯ ዶክተር መቅደስ ከመስከረም 2015 ጀምሮ ይህ ስልጣን እስኪሰጣቸው ድረስ የዓለም ጤና ድርጅት ባልደረባ ሆነው እንደሰሩ የሊንክድኢን ገጻቸው ያመለክተዋል።

ከዚያ ቀደም ብሎ ደግሞ በጳውሎስ ሚሊኒየም ኮሌጅ ከ2010 ጀምሮ የማህጸን እና ጽንስ ተባባሪ ፕሮፌሰር ሆነው እየሰሩ ነበር።

በሌላ በኩል ከየካቲት 2012 ጀምሮ ለሁለት ዓመታት የኢትዮጵያ ጽንስ እና ማህጸን ሃኪሞች ማህበር ፕሬዝዳንት ሆነው ያገለገሉ ሲሆን ከዚያ በኋላ ደግሞ ከመስከረም 2014 እስከ 2015 ዓ.ም የዓለም አቀፍ ስነ ተዋልዶ ጤና ስልጠና ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ሆነው ሰርተዋል።

በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህር እና የጽንስ እና ማህጸን ትምህርት ክፍል ውስጥም ከአምስት ዓመታት በላይ ሰርተዋል።

ዶክተር መቅደስ ዳባ በሀዋሳ የኒቨርሲቲ በህክምና ዶክትሬት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያገኙ ሲሆን ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በህብረተሰብ ጤና ማግኘታቸውን ለምክር ቤቱ ዕጩ አደርገው ያቀረቧቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ተናግረዋል።

ቀጥሎም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጽንስ እና ማህጸን ሃኪም ሆነው ተመርቀዋል።

ከዚያም በኋላ በቅዱስ ጳውሎስ ሚለኒየም ሜዲካል ኮለጅ በቤተሰብ ምጣኔ እና ስነ ተዋልዶ ጤና ላይ አተኩረው ተምረዋል።

ባለትዳር እና የሁለት ልጆች እናት የሆኑት ዶክትር መቅደስ የገዢው ፓርቲ ብልጽግና ፓርቲ አባል እንዳልሆኑ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በጤናው ዘርፍ ባደረጉት አስተዋጽኦ ባሳዩት የላቀ ችሎታ እና ብቃትም ተመርጠው እንደሆነም ተናግረዋል።