አርሰናል ማንቸስተር ዩናይትድን በመርታት የዋንጫ ግስጋሴውን ቀጥሏል

ታትሟል

አርሰናል ኤሜሬትስ ላይ በተካሄደው በድርጊት የታጀበ ግጥሚያ ዩናይትድን በመርታት ዋንጫ ለማንሳት የሚያደርገውን ግስጋሴ ቀጥሏል።

ኤዲ ኒኬቲያህ በ90ኛው ደቂቃ ያስቆጠራት ግብ አርሰናል ሦስት ነጥብ እንዲያካብት ምክንያት ሆናለች።

ከዚህ ጨዋታ ቀደም ብሎ ማንቸስተር ሲቲ ዎልቭስን ማሸነፉን ተከትሎ አርሰናል ጫና በርክቶበት ነበር።

ነገር ግን ከዩናይትድ ጋር በነበረበት ጨዋታ ቀድሞ ጎል ቢገባበትም ይህንን በመቀልበስ አንድ ጨዋታ እየቀረው በአምስት ነጥብ ልዩነት ሊጉን መምራት ችሏል።

የማንቸስተር ዩናይትድ ኮከብ ማርከስ ራሽፈርድ በ17ኛው ደቂቃ በቀኝ እግሩ ከርቀት የለጋት ኳስ የመጀመሪያው የጨዋታው ጎል ሆናለች።

ቢሆንም አርሰናሎች ከሰባት ደቂቃ በኋላ በኤዲ ኒኬቲያህ አማካይነት አቻ መሆን ችለዋል።

ከእረፍት በኋላ ቡካዮ ሳካ በግራ እግሩ ከበረኛው ክልል ውጪ የሰደዳት ኳስ አርሰናልን ወደ መሪነት ብታመጣም ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ ሊሳንድሮ ማርቲኔዝ በግምባር የገጫት ኳስ ጨዋታው ሁለት እኩል እንዲሆን አስችላለች።

በጨዋታው መገባደጃ አርሰናሎች ጨዋታውን ለመርታት ብዙ ሲያጠቁ ቢታዩም የዩናይትድ መከላከለን ጥሰው መግባት ተስኗቸው አምሽቶ ነበር።

የማንቸስት ዩናይትዱ በረኛ ዴቪድ ዴ ሂያ የአርሰናሉ አጥቂ ኒኬቲያህ ወደ ጎል የሰደዳትን ኳስ በድንቅ ሁኔታ አድኖበታል።

ነገር ግን አርሰናል የፈጠረው ጫና በስተመጨረሻ ፍሬ አፈራ።

ጋብርኤል ጂሰስ መጎዳቱን ተከትሎ እሱን ተክቶ የአጥቂ ሥፍራውን የተቆጣጠረው ኤዲ ኒኬቲያህ በ90ኛው ደቂቃ ወደ ጎል የሸረፋት ኳስ ኤሜሬትስ በደስታ እንዲናወጥ ምክንያት ሆናለች።

ምንም እንኳ ከዩናይትድ ጋር አቻ መለያየት ክፉ የሚባል ውጤት ባይሆንም ማሸነፍ ለአርሰናል ከሦስት ነጥብም በላይ ነው።

ማንቸስተር ሲቲ ማሸነፉና ራሽፈርድ አስቆድሞ ጎል ማስቆጠሩ አርሰናል ላይ ጫናውን ቢያበረታም የማይክል አርቴታት ልጆች በዚህ ሳይደናገሩ ተጠባቂውን ጨዋታ መርታት ችለዋል።

ሳካና አምበሉ ማርቲን ኦዴጋርድ እንደተለመደው በጣም ድንቅ የሆነ ችሎታቸውን ሲያሳዩን አምሽተዋል።

ማንቸስተር ዩናይትድ በሊሳንድሮ ማርቲኔዝ እየተመሩ የመከላከል ሥራቸውን እንደጨረሱ ባመኑበት ወቅት ነው አርሰናል የማሸነፊያዋን ጎል ያስቆጠረው።

የብራዚላዊው ተከላካይ አማካይ ካዜሚሮ በቅጣት ምክንያት በጨዋታው አለመሰለፍ ለማንቸስተር ዩናይትድ ትልቅ ጉዳት ሆኖ ተገኝቷል።

ያም ሆኖ ዩናይትዶች በሳካ ጎል ምክንያት መሪነቱን ቢነጠቁም አቻ ለመሆን ጎል ካስቆጠሩ በኋላ ጨዋታውን በአቻ ለማጠናቀቅ ያሳዩት ተጋድሎ ድንቅ ነበር።

ይህንን ጨዋታ ተከትሎ 19 ጨዋታዎች ያደረገው አርሰናል በ50 ነጥብ ሊጉን እየመራ ይገኛል።

ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ማንቸስተር ሲቲዎች 20 ጨዋታዎች አድርገው ከአርሰናል በአምስት ነጥብ ዝቅ ብለው ተቀምጠዋል።

ኒውካስትል እና ማንቸስተር ዩናይትድ በተከታታይ በእኩል 39 ነጥብ ሦስተኛ እና አራተኛ ደረጃን ይዘዋል።

ዛሬ ምሽት ከፉልሃም የሚፋለመው ቶተንሃም ሆትስፐርስ በ33 ነጥብ አምስተኛ ደረጃ፤ ብራይተን ደግሞ በ31 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

ቅዳሜ ዕለት ተገናኝተው ያለምንም ግብ የተለያዩት ሊቨርፑል እና ቼልሲ 9ኛ እና 10ኛ ደረጃን ተቆናጠዋል።