አሜሪካ በእስራኤል የሚገኝ ኤምባሲዋን ለማፈንዳት ሞክሯል ያለችውን ግለሰብ በቁጥጥር ስር አዋለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሜሪካ በእስራኤል፣ ቴልአቪቭ የሚገኝ ኤምባሲዋን በተቀጣጣይ ፈንጅ ለማፈንዳት ሞክሯል ያለችውን የአሜሪካ እና የጀርመን ጥምር ዜግነት ያለውን ግለሰብ እሁድ፣ ግንቦት 17/ 2017 ዓ.ም በቁጥጥር ስር ማዋሏን አስታወቀቸ።
የ28 ዓመቱ ጆሴፍ ኒውማየር በኒውዮርክ ጆን ኤፍ ኬኔዲ አየር ማረፊያ በቁጥጥር ስር መዋሉን የአገሪቱ የፍትህ ሚኒስቴር ባለስልጣናት ገልጸዋል።
በኤምባሲው አቅራቢያው ተቀጣጣይ ቁሶችን በቦርሳው ይዞ ከተገኘ በኋላ በእስራኤል ባለስልጣናት ከአገሪቱ ከተባረረ በኋላ በአሜሪካ መያዙ ተነግሯል።
ግለሰቡ እሁድ ዕለት ፍርድ ቤት የቀረበ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በእስር ላይ እንደሚገኝ የፍትህ ሚኒስቴር አስታውቋል።
"ተከሳሹ በእስራኤል በሚገኘው ኤምባሲያችን ላይ ያለመ አሰቃቂ ጥቃት በማቀድ፣ አሜሪካውያንን በሞት በማስፈራራት እንዲሁም በፕሬዚዳንት ትራምፕ ህይወት ላይ በማነጣጠር" መከሰሱን ጠቅላይ አቃቤ ህግ ፓሜላ ቦንዲ ገልጸዋል።
ግለሰቡ በቁጥጥር ስር የዋለው አንድ ግለሰብ በዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው የአይሁድ ሙዚየም ደጃፍ ላይ ሁለት የእስራኤል ኤምባሲ ሰራተኞችን ከገደለ ከጥቂት ቀናት በኋላ ነው።
የአሜሪካ የፌደራል ባለስልጣናት ተከሳሹ በእስራኤል ሚያዝያ ወር ላይ እስራኤል እንደገባ እና ግንቦት 11 ዕለት ጥቁር ቦርሳ አዝሎ በቴልአቪቭ ወደሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ አቅንቷል ብለዋል።
ግለሰቡ በኤምባሲው በር ሲያልፍ በጥበቃው ላይ ምራቁን መትፋቱን የፍትህ መስሪያ ቤቱ አክሏል።
ጥበቃው ሊይዘው ሲሞክር ጆሴፍ ቦርሳውን ትቶ ሮጧል ተብሏል።
በቦርሳው ውስጥ ከተቀጣጣይ ፈሳሾች የተሰሩ ሶስት ፈንጂዎች የተገኙ ሲሆን ከተወረወሩ በኋላም ከፍተኛ እሳት የሚያስነሱ ናቸው ተብሏል።
ፖሊስ በኋላ ግለሰቡን በሆቴሉ ካገኘው በኋላ በቁጥጥር ስር አውሎታል።
ጆሴፍ በማህበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ በቴል አቪቭ የሚገኘውን ኤምባሲ ለማቃጠል ቃል መግባቱን ከማስፈር በተጨማሪ "ሞት ለአሜሪካ እና ለአሜሪካውያን" የሚል ጥሪ ማድረጉን ባለስልጣናቱ አክለዋል።
በተጨማሪም ከግለሰቡ ጋር ግንኙነት አለው ተብሎ በሚታመን ሌላ የማህበራዊ ድረ ገጽ ላይ ትራምፕን ለመግደል መዛቱም ተነግሯል።
ተከሳሹ እሁድ ዕለት ወደ አሜሪካ ከተላከ በኋላ በቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን፤ ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ የ20 ዓመት እስራት እንደሚጠብቀው ተገልጿል።
ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ሁለት ወጣት ጥንዶች ያሮን ሊቺንስኪ እና ሳራ ሊን ሚልግሪም በዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው የካቲታል አይሁድ ሙዚየም ደጃፍ ላይ በጥይት መገደላቸው ይታወሳል።
ፖሊስ ተጠርጣሪ ነው ያለው የ30 ዓመቱ ኤሊያስ ሮድሪጌዝ ጥንዶቹ ላይ ከተኮሰ በኋላ "ፍልስጤም ነጻ ትውጣ" ሲል መጮሁ ተዘግቧል።
የአሜሪካ የሀገር ውስጥ ደኅንነት ፀሐፊ ክሪስቲ ኖም ለተገደሉት ጥንዶች ሰኞ ዕለት እስራኤል በሚደረገው መታሰቢያ ስነ ስርዓት ላይ ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።












