በናይጄሪያ አንዲት ዶክተር መታገቷን ተከትሎ ሃኪሞች የሥራ ማቆም አድማ መቱ

የሃኪሟ ፎቶ እንድትለቀቅ ከሚጠይቅ ጽሁፍ ጋር በማህብራዊ ሚዲያ እየተጋራ ነው

የፎቶው ባለመብት, NARD

የምስሉ መግለጫ, የሃኪሟ ፎቶ እንድትለቀቅ ከሚጠይቅ ጽሁፍ ጋር በማህብራዊ ሚዲያ እየተጋራ ነው
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በናይጄሪያ በታጋቾች ከተያዘች 8 ወራት ያስቆጠረችው ዶክተር ጋናያት ፖፑላ የተባለች የጤና ባለሙያ እንድትለቀቅ በመጠየቅ በአገሪቱ የመንግሥት ሆስፒታል የሚሰሩ ሃኪሞች ለ7 ቀናት የሚቆይ የሥራ ማቆም አድማ ጀምረዋል።

የአምስት ልጆች እናት የሆነችው ዶክተር ባለፈው ታህሳስ ወር በእኩለ ሌሊት ከባለቤቷ እና የወንድሟ/የእህቷ ልጅ ጋር በአጋቾች ተወስዳለች።

ባለቤቷ ባለፈው መጋቢት ወር በአጋቾች የተጠየቀውን ገንዘብ ከፍሎ እንደተለቀቀ የተነገረ ሲሆን የዐይን ሃኪሟ እና ዘመዷ ግን አሁንም በአጋቾቹ እጅ ላይ ይገኛሉ።

በዚህ ሳቢያ ከፍተኛ ቁጣ ውስጥ የሚገኙት የናይጀሪያ ሃኪሞች በሥራ ማቆም አድማው የአደጋ ወይም የአስቸኳይ ጊዜ ህክምና አገልግሎት ጭምር እንደማይሰጡ ገልጸዋል።

ሀኪሞች የጸጥታ ተቋማት ዶክትር ፑፖላን ለመታደግ በቂ ሥራ አልሠሩም ብለዋል።

የናይጀሪያ ሀኪሞች ማኅበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ዴሌ አብዱላሂ በሀኪሟ እገታ ሳቢያ ቤተሰቦቿ እና የሥራ ባልደረቦቿ ላለፉት ስምንት ወራት ጭንቅ ላይ ናቸው ብሏል።

በናይጀሪያ የሀኪሞች ህይወት ግድ ሊሰጥ ይገባል የሚለው ፕሬዝዳንቱ በዚህኛው አድማ ለውጥ የማይመጣ ከሆነ ቀነ ገደብ የማይቀመጥለት አድማ ሃኪሞች እንደመሚቱ ጨምሮ ገልጿል።

የታጋቿ የሥራ ባልደረባዋ የሆነው ዶክተር ኢብራሂም መሃመድ ኦፓካናኪ ሃኪሞች “ሞራላቸው እየተነካ እና እንዲሸበሩ እየተደረጉ ቆይተዋል። ሃኪሞች ደህንንነታቸው ተጠብቆ ሊሰሩ ይገባል” ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

እንደባልደረባዋ ገለጻ በእገታ ላይ የምትገኘው ሃኪም በብሔራዊ የዐይን ህክምና ማዕከል ላለፉት ስድት ዓመት ሰርታለች።

ባልደረባዋ ትጉ ባለሙያ እና በቤተሰቧ ውስጥ ደግሞ ኃላፊነት የሚሰማት ሴት ነች ሲል ገልጿታል።

ዶክተር ጋናያት ፖፑላ በታጋቾች በተወሰደችበት ጊዜ የመጨረሻ ልጇን የምታጠባ እናት ነበረች።

በናይጄሪያ ምዕራባዊ ክፍል ባለው ካዱና ግዛት የሚገኘው የዐይን ሆስፒታል በሀገሪቱ ከሚገኙ ቅልቅ ሆስፒታሎች አንዱ ነው።

ሆስፒታሉ ከከተማ መውጪያ ላይ መገኘቱ አጋቾች ተጠቂዎችን በቀላሉ ኢላማ እንዲያደርጉ እንደረዳቸው ይነገራል።

የሀኪሟ መኖሪያ ቤትም በሆስፒታሉ ክልል ውስጥ የሚገኝ ነው።

ከ3 ዓመት በፊትም በርከታ ተማሪዎች ከዚህ ሆስፒታል አቅራቢያ ወደ ሚገኝ ጫካ ታግተው ተወስደው ነበር።

የዶክተር ፑፖላ አጋቾች 40 ሚሊዮን ናይራ ወይም ወደ 25 ሺህ ዶላር የሚሆን ገንዘብ ለማስለቀቂያ ጠይቀዋል።

በናይጄሪያ ከአውሮፓውያኑ 2022 ወዲህ ተግባራዊ የሆነ ህግ ታጋቾችን ለማስለቀቅ በሚል ለአጋቾች መክፈል ወንጀል አድርጎ ደንግጓል። ሆኖም በርካቶች ወዳጅ ዘመዶቻቸውን ለማስለቀቅ አሁንም ክፍያ ይፈጽማሉ።

ህጉ የማስለቀቂያ ገንዘብ የሚከፍሉ ሰዎች እስከ 15 ዓመት እንደሚፈረድባቸው ይገልጻል ሆኖም እስካሁን አንድም ሰው በዚህ ወንጀል ጥፋተኛ አልተባለም።

መንግስት በህክምና ባለሙያዎቹ የሥራ ማቆም አድማ ላይም ሆነ በታገችው ሃኪም ጉዳይ እስካሁን ያለው ነገር የለም።

ገንዘብ ከፍሎ እንደተለቀቀ የተነገረው ባለቤቷም ለመገናኛ ብዙሃን አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል።

የሃኪሞች ማህብር ፕሬዝዳንቱ ዶክተር አብዱላሂ ቤተሰቦቿ ቀድም ብሎ ሁኔታዎች በተለሳለሰ መንገድ እንዲሄዱ እየሞከሩ እንደነበር ገልጾ አሁን ግን ጉዳዩን ወደ ሃኪሞች ማህበር መውሰዳቸውን ገልጿል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እገታ በናይጄሪያ እጅግ እየተለመደ መጥቷል። በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በወንጀለኛ ቡድኖች የታገቱ ሲሆን አጋቾች ይህንን ድርጊት ቀላል ገንዘብ ማግኛ መንገድ አድርገውታል። ይህ ሁኔታ ደግሞ በሀገሪቱ ምዕራባዊ ክፍል እጅግ የከፋ ነው።