ሩሲያ በበርካታ አገራት ጫና ለማሳደር 300 ሚሊዮን ዶላር ወጪ አድርጋለች ተባለ

ታትሟል

ሩሲያ ከእአአ 2014 ጀመሮ ከ24 አገራት በላይ በሚገኙ ፖለቲከኞች ላይ ጫና ለመፍጠር 300 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ማድረጓን አሜሪካ ገለጸች።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ይህ መረጃ የተገኘው ትናንት ማክሰኞ መስከረም 3/2015 ዓ.ም. ይፋ ከተደረገ የደኅንነት መረጃ ነው ብሏል።

የፕሬዝዳንት ባይደን አስተዳደር ከፍተኛ ባለሥልጣን ይህ ገና ጅማሮ እንጂ የሞስኮን ጫና ሙሉ ምሥል አያሳይም ብለዋል።

ሩሲያ እስካሁን በጉዳዩ ላይ ያለችው ነገር ባይኖርም ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ አሜሪካ  በሌሎች አገራት ጉዳዮች ላይ ጣልቃ ትገባለች ስትል ትከሳለች።

ይህ የአሜሪካ መንግሥት ይፋ ያደረገው የደኅንነት መረጃ የሩሲያ ጫና ውስጥ ገብተዋል የተባሉት ፖለቲከኞች ስም ዝርዝርም ይሁን ጫና አርፎባቸዋል የተባሉ አገራትን ይፋ አላደረገም።

ይሁን እንጂ አገራቱ በአራት አህጉራት የሚገኙ ናቸው ተብሏል።

በስም ያልተጠቀሱት የባይደን አስተዳደር ከፍተኛ ባለሥልጣን ሞስኮ ጫና አሳድራባቸዋለች የተባሉት ፖለቲከኞች ለሚገኙባቸው የተመረጡ አገራት መንግሥታት አሜሪካ ገለጻ እያደረገች ነው ብለዋል።

አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ በበኩሉ የአሜሪካ ባለሥልጣናትን ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ ሩሲያ እአአ 2017 ላይ የአልባኒያውን ዲሞክራቲክ ፓርቲ ለመደገፍ ግማሽ ሚሊዮን ዶላር ወጪ አድርጋለች።

እንደ ኤኤፍፒ ምንጮች ከሆነ ሞስኮ በቦስኒያ፣ ሞንቴኔግሮ እና ማደጋስካር የሚገኙ ዕጩ ፖለቲከኞችን አልያም ደግሞ ፓርቲዎችን በገንዘብ ደግፋለች።

ሞስኮ ዋና መቀመጫዋን ቤልጂየም ብራሰልስ በማድረግ ሐሰተኛ በሆኑ ኩባንያዎች አማካይነት በአውሮፓ አገራት ለሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ገንዘብ በመስጠት ጫና ለማሳደር ጥረት ታደርጋለች ተብሏል።

ሞስኮ ከዚህ ቀደም የአሜሪካ የስለላ ተቋም ሲአይኤ መፈንቅለ መንግሥቶችን በመደገፍ ጭምር በሌሎች አገራት ጉዳዮች እጁን ያስገባል ብላ ነበር።

በካርኔይጅ ሜለን ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪው ዶቭ ሌቪን የተሰባሰቡ መረጃዎች ከእአአ 1946-2000 አሜሪካ መፈንቅለ መንግሥት ወይም የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራን ሳይጨምር በመላው ዓለም በሚገኙ ከ80 በላይ አገራት የውጭ ጉዳዮች ላይ ጣልቃ መግባቷን ያሳያል።

ትናንት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ የሩሲያን ጣልቃ ገብነት “በሉዓላዊነት ላይ የሚቃጣ ጥቃት ነው” ሲሉ ገልጸውታል።

የአሜሪካ የደኅንነት ባለሥልጣናት ሞስኮ እአአ በ2020 በተካሄው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዶናልድ ትራምፕ እንዲያሸንፉ ቭላድሚር ፑቲን ጫና እንዲፈጠር አዘዋል የሚል ሪፖርትን ገምግመው ነበር።

ይሁን እንጂ የደኅንነት ባለሥልጣናቱ በመጨረሻ የምርጫ ውጤቱ በሌላ አገር ተጽዕኖ ሥር አልወደቀም ብለዋል።

ሞስኮ ይህን ከስ “መሠረተ የሌላው” ስትል አጣጥላው ነበር።