የዩክሬን ስደተኞች በክረምቱ ወራት በያሉበት አገራት እንዲቆዩ ተጠየቁ

7.7 ሚሊዮን የሚሆኑ ዩክሬናዊያን ሩስያን ጨምሮ ወደተለያዩ የአውሮፓ አገራት ተሰደዋል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ወደተለያዩ የአለም አገራት የተሰደዱ ዩክሬናዊያን መጪው ክረምት እስከሚያልፍ ድረስ በስደት ባሉባቸው አገራት እንዲቆዩ ተጠየቁ።

በኃይል ማሰራጫ ስርዓቶች ላይ ጦርነቱ ያስከተለውን ጫና ለመቋቋም በማሰብ ብሎም ሩሲያ ጥቃቷን አጠናክራ ትቀጥላለች የሚለው ስጋት ለዚህ እንደምክንያት ተቀምጧል።

አሁን ያለው መሠረተ ልማት ተጨማሪ ጫናዎችን መቋቋም አይችልም ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሯ አይሪና ቬሬሽቹክ ተናግረዋል።

''ሩሲያ ምን እያደረገች እንደሆነ እያያችሁ ነው። ይህንን ክረምት ማለፍ አለብን'' ሲሉም አክለዋል።

የዩክሬኑ ፕሬዘዳንት ቮሎድሜር ዜለንስኪ የሩሲያ የአየር ጥቃቶች የአገራቸውን የኃይል አቅርቦት ዘረፍ አንድ ሶስተኛውን ማውደሙን ተናግረዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሯ ቬሬሽቹክ በበኩላቸው ምንም እንኳን ዩክሬናዊያን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ፍላጎት ቢኖራቸውም ለግዜው ግን ይህንን ከማድረግ እንዲቆጠቡ ጠይቀዋል።

አክለውም ''አሁን ያለው ሁኔታ ከመባባስ ውጪ አይሻሻልም'' ሲሉም ተናግረዋል። ''ከቻላችሁ ለግዜው በውጪ አገራት ቆዩ'' ሲሉም ተናግረዋል።

የዩክሬን ኢኮኖሚ ጦርነቱን ተከትሎ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል። ፕሬዝዳንት ዜለንስኪ የቀጣይ ዓመት የአገሪቱ በጀት ላይ ያጋጥማል ተብሎ የሚጠበቀውን 38 ቢሊዮን ዶላር የበጀት ጉድለት ለመሙላት ድጋፍ ከመላው ዓለም ጠይቀዋል።

ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ተቋም አይኤምኤፍ በበኩሉ ዩክሬን በቀጣዩ ዓመት በወር 3 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ያስፈልጋታል ብሏል። የሞስኮ ድብደባ ተባብሶ ከቀጠለ ደግሞ ይህ ወደ 5 ቢሊዮን ዶላር በወር ከፍ ሊል እንደሚችል አስጠንቅቋል።

ምዕራባዊቷ ሊቪቭ ከተማ ከንቲባ የሆኑት ሰርሂ ኪራል ባሳለፍነው ቅዳሜ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ሩሲያ ከመጪው ክረምት በፊት ዋና ዋና መሠረተ ልማቶችን የማውደም ስልት እየተከተለች ነው ሲሉ ከሰዋል። ይህንንም ተከትሎ ጦርነቱን ከጦር ሜዳ ባሻገር የማምጣት እቅድ አላት ሲሉ ከሰዋል።

ሩስያ የዩክሬንን የኃይል መሠረተ ልማቶች ማጥቃት የጀመርኩት በቅርቡ ክሬሚያን ከዋናው የሩሲያ ጋር የሚያገናኛውን ድልድይ ላይ ለደረሰው ጉዳት ምላሽ ለመስጠት ነው በሚል አስተባብላለች። ነገር ግን እስካሁን ድረስ ዩክሬን ለዚህ ጥቃት ኃላፊነቱን አልወሰደችም።

ባሳለፍነው አርብ ፕሬዝዳንት ዜለንስኪ በሩስያ ቁጥጥር ስር በሚገኘው ደቡባዊ ዩክሬን ኬርሰን ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኘውን የኃይል ማመንጫ ግድብ ለማፍረስ ፈንጂ አጥምዳለች ሲሉ ሩስያን ከሰዋል።

ግድቡ ላይ ፍንዳታ የሚከሰት ከሆነ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት አደጋ ላይ እንደሚወድቅ ፕሬዝዳንቱ ተናግረው ነበር።

ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ 44 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ካላት ዩክሬን 7.7 ሚሊዮን የሚሆኑ ዩክሬናዊያን ሩሲያን ጨምሮ ወደተለያዩ የአውሮፓ አገራት መሰደዳቸውን የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኤጀንሲ ይፋ ያደረገው ቁጥር ያመላክታል።