ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከ60 በላይ ስደተኞች በኬፕ ቨርዴ ባህር ዳርቻ ሳይሞቱ እንዳልቀረ ተገለጸ
በምዕራብ አፍሪካ ኬፕ ቨርዴ ባህር ዳርቻ ስደተኞችን አሳፍራ የነበረች ጀልባ ተንሳፋ ከተገኘች በኋላ ከ60 በላይ ስደተኞች ሳይሞቱ እንዳልቀረ ተገለጸ።
ሕጻናትን ጨምሮ 38 ሰዎች ከሞት የተረፉ ሲሆን በሳል ደሴት አንዳንዶች በስትሬቸር ላይ ሆነው እርዳታ ሲደረግላቸው በተንቀሳቃሽ ምስሎች ታይተዋል።
ከአንድ ወር በላይ በባህሩ ላይ በነበረችው ጀልባ ላይ ተሳፍረው የነበሩት ሁሉም ስደተኞች ከሴኔጋል የተነሱ ናቸው ተብሏል።
ጀልባዋ መጀመሪያ ላይ የታየችው ሰኞ ዕለት መሆኑን ፖሊስ ለፈረንሳዩ የዜና ወኪል (ኤኤፍፒ) ተናግሯል።
አደጋውን አስመልክቶ የወጡ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቶችም፣ ጀልባዋ ሰምጣ እንደነበርና በኋላ ላይ ተንሳፋ መገኘቷን አመልክተዋል።
በእንጨት የተሰራችው ጀልባ፣ የኬፕ ቨርዴ ክፍል ከሆነው ሳል ደሴት 320 ኪሎ ሜትር በሚጠጋ ርቀት ላይ በስፔናዊው አሳ ማጥመጃ ጀልባ የታየች ሲሆን ለባለሥልጣናት መጠቆሙን ፖሊስ ገልጿል።
ከአደጋው ከተረፉት መካከል እድሜያቸው ከ12-16 የሚሆኑ ሕጻናት እንደሚገኙበት የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) ቃል አቀባይ ተናግረዋል።
የኬፕ ቨርዴ ባለሥልጣናት ተጨማሪ የሰው ሕይወት እንዳይጠፋ ቀድሞ ለመከላከል በስደት ላይ ዓለም አቀፍ እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀዋል።
የሴኔጋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማክሰኞ ዕለት ከአደጋው የተረፉትን ሰዎች ጠቅሶ እንደገለጸው፣ ጀልባዋ ከሴኔጋል ፋሴ ቦይ ከሚባል መንደር 101 ሰዎች አሳፍራ የተነሳቸው በአውሮፓውያኑ ሐምሌ 10 ላይ ነው።
ስደተኞቹ በተነሱበት መንደር ተመራጭ የሆኑት ባለሥልጣን ሞዳ ሳምብ በበኩላቸው በጀልባዋ ላይ የነበሩት ሁሉም በሚባል ደረጃ ያደጉት በመንደሯ ውስጥ እንደሆነ ገልጸው፤ የተወሰኑ ቤተሰቦችም ከአደጋው ከተረፉት መካከል የእነርሱ የቤተሰብ አባላት ይገኙበት እንደሆነ ለማወቅ እየተጠባባቁ መሆናቸውን ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
ሚኒስቴሩ ከሞት የተረፉ ሴኔጋላውያንን ወደ አገራቸው ለመመለስ ከኬፕ ቨርዴ ባለሥልጣናት ጋር እየሰሩ እንደሆነም ገልጿል።
ከስደተኞቹ መካከል የሴራሊዮን እና አንድ የጊኒ ቢሳው ዜጋ ይገኙበታል።
የሳል የጤና ባለሥልጣን ጆሴ ሞሬራ እንዳሉት ከአደጋው የተረፉት እያገገሙ እንደሆነ እና እየተከታተሏቸው እንዳለ ገልጸዋል።
ጤና ሚኒስትሩ ፊሎሜና ጎንካልቭስ በበኩላቸው “ስደት ዓለም አቀፍ ትብብርን፣ ውይይትንና ዓለም አቀፍ ስልትን የሚጠይቅ ጉዳይ እንደሆነ እናውቃለን። በመሆኑም ሁላችንም ፣ ሁሉም አገራት በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠን ሌላ ሕይወት እንዳይጠፋ ምን ማድረግ እንደምንችል መነጋገር አለብን “ ብለዋል።
የአይኦኤም ቃል አቀባይ ሳፋ ምሰህሊ “ለስደት ደኅንነቱ የተጠበቀ መሸጋገሪያ የለም።ይህ ባለመኖሩም ሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ስደተኞችን አደገኛ በሆነ ጉዞ ውስጥ እንዲያልፉ እንዲያደርጉ ክፍተት ፈጥሯል" ብለዋል።
ከአደጋው የተረፉ ሰዎች አሁን ላይ በኬፕ ቨርዴ ጉዟቸው ቢገታም የሚፈልጉት መዳረሻ ግን አይደለም።
እንደ ድርጅቱ ከሆነ ይህ መንገድ ስደተኞች ከምዕራብ አፍሪካ ተነስተው ወደ ስፔን ግዛት ከዚያም ወደ ሌሎች አውሮፓ አገራት ለመግባት የሚጠቀሙበት አንደኛው አደገኛ መንገድ ነው።
በዚህ መንገድ የሚሰደዱ ስደተኞችን ትክክለኛ ቁጥር ማወቅ ባይቻልም በ2020 እና በ2023 መካከል ባሉት ዓመታት ውስጥ ቢያንስ 67 ሺህ ሰዎች በካናርይ ደሴቶች መድረሳቸው ተገልጿል።
በእነዚሁ ዓመታትም ከ2 ሺህ 500 በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።
አይኦኤም ይህ ቁጥር በድርጅቱ የተመዘገበውን ብቻ የሚያመልክት መሆኑን ገልጾ፣ በምስጢርና መደበኛ ባልሆኑ መንገዶች የሚደረጉ ጉዞዎች በመኖራቸው ቁጥሩ ከፍተኛ እንደሚሆን ጠቁሟል።