የፓኪስታን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ከግድያ ሙከራ አመለጡ

የፎቶው ባለመብት, RAHAT DAR/EPA-EFE/REX/Shutterstock
ከሥልጣን የተወገዱት የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ካን በምሥራቃዊ ዋዚራባድ የተቃውሞ ሰልፍ ሲመሩ በተከፈተባቸው የተኩስ እሩምታ ጉዳት አጋጠማቸው።
ካን በተሽከርካሪያቸው ላይ የተኩስ እሩምታ ተከፍቶ በደረሰው ጥቃት እግራቸው ላይ ጉዳት አጋጥሟቸዋል። በጥቃቱ አንድ ሰው የተገደለ ሲሆን ቢያንስ አምስት ሰዎች ቆስለዋል።
የጥቃቱን ዓላማ በተመለከተ ከባለሥልጣናት የተሰጠ አስተያየት ባይኖርም ደጋፊዎቻቸው ግን የግድያ ሙከራ ነው ብለዋል።
የተቃውሞ ሰልፉ የተጠራው በመንግሥት ከተያዘው እቅድ ቀድሞ ምርጫ እንዲካሄድ ለመጠየቅ ነበር።
የ70 ዓመቱ ካን፣ በዋና መዲናዋ ኢስላማባድ ለማጠናቀቅ የታሰበውን ሰልፍ እየመሩ ነበር ተኩሱ የተከፈተው።
የቀድሞው ዓለም አቀፍ የክሪኬት ኮከቡ ፖለቲከኛ ወደ ላሆር ሆስፒታል ተወስደዋል። የፓርቲያቸው ቃል አቀባይ እንዳሉት፣ ካን ጉዳት ያጋጠማቸው ከጉልበታቸው በታች ባለው የእግራቸው ክፍል ላይ ነው።
ካን አሁን ላይ በጥሩ ጤንነት ላይ እንደሚገኙ የገለጹ ሲሆን ቀዶ ሕክምና ሳይደረግላቸው እንደማይቀር ረዳታቸው ተናግረዋል።
ፖሊስ የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር "ለመግደል ሞክሯል" ሲል በቁጥጥር ሥር ያዋለው ግለሰብ የሰጠውን ቃል የሚያሳይ ቪዲዮ አጋርቷል።
ፖሊስ ቃለ ምልልሱን ያደረገው በምን ሁኔታ እንደሆነ ግልጽ አይደለም። ሆኖም በቪዲዮው ላይ ግለሰቡ ለምን ተኩስ እንደከፈተ በፖሊስ ሲጠየቅ “ሕዝቡን እያሳሳተ ነው። ልገድለው እፈልግ ነበር። በመሆኑም ልገድለው ሞክሬያለሁ” ሲል ምላሽ ሰጥቷል።
የካን ዋና ረዳት እና ቃል አቀባይ በበኩላቸው “የፓኪስታን መንግሥት በቀጥታ በጥቃቱ ተሳትፏል።” ሲሉ ለቢቢሲ ኒውስ አዎር ፕሮግራም ተናግረዋል።
ቃል አቀባዩ ራኦፍ ሃሰን፣ መንግሥት ኢምራን ካንን ለማጥፋት እየሞከረ ነው ያሉ ሲሆን፣ መንግሥት የለቀቀውን ቪዲዮ “መሸፋፈኛ ” ሲሉ አጣጥለውታል።
ቢቢሲ የፓኪስታን መንግሥት በቀረበበት ክስ ላይ ምላሽ እንዲሰጥ ጠይቋል።
ከሥፍራው የወጣው ቪዲዮው የሚያሳየው ካን እና ደጋፊዎቻቸው ተኩስ ከመሰማቱ በፊት ተሽከርካሪ ላይ ሆነው ሰልፍ ሲመሩ ያሳያል። ከዚያም ተኩሱ ሲሰማ ካን ወደ መሬት ዝቅ ያሉ ሲሆን በዙሪያቸው የነበሩ ሰዎች እርሳቸውን ለመከለል ሲሞክሩ ታይተዋል።
ሌላኛው ቪዲዮ ደግሞ ካን ከተኩሱ በኋላ ቀኝ እግራቸው በፋሻ ታስሮ በመኪና ሲወሰዱ አሳይቷል።
የፒቲአይ ፓርቲ አባልም ፊታቸው በፋሻ ተጠቅልሎ እና ልብሳቸው በደም ተለውሶ ሰዎች ለካን እና ለተጎዱት በሙሉ መጸለይ እንዳለባቸው ሲናገሩ ይሰማል።
አሁን በሥልጣን ላይ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ሸህባዝ ሻሪፍ፣ ጥቃቱን ያወገዙ ሲሆን አስቸኳይ ምርመራ እንዲደረግም አዝዘዋል።ፕሬዝዳንት አሪፍ አልቪ በበኩላቸው ክስተቱን “ አስከፊ የግድያ ሙከራ ነው “ ብለውታል።
ጥቃቱ ሲፈፀም የተመለከተ የአካባቢው ጋዜጠኛ ዞሪያዝ ባንጋሽ ለቢቢሲ እንደተናገረው፣ ተኩሱ የተጀመረው ካን ሰልፉን መምራት ሲጀምሩ ሲሆን ተኩስ የተሰማውም በድንገት ነበር። ከዚያም አንድ ግለሰብ ሽጉጥ ይዞ እንደተመለከቱ እና የተኮሰው ጥይት አንዳንድ የፓርቲ አመራሮች እና ካን ላይ ማረፉን ተናግሯል።
ካን ጥቃቱ የተፈፀመባቸው አዲስ ምርጫ እንዲካሄድ ለመጠየቅ በዚህ ዓመት ለሁለተኛ ጊዜ የተካሄደውንና ላለፉት ሰባት ቀናት የዘለቀውን ሰልፍ እየመሩ ባለበት ወቅት ነው።
መንግሥት በታቀደው መሠረት በሚቀጥለው ዓመት ምርጫ እንደሚያካሂድ በተደጋጋሚ ገልጿል።
ባለፈው ወር የፓኪስታን የምርጫ ኮሚሽን ካንን ከፖለቲካ ሹመት አግዷቸዋል።
ካን ከውጭ አገር ባለሥልጣናት ስጦታዎችን እና ሙስና በመቀበል ይከሰሳሉ። ስጦታዎቹ የሮሌክስ ሰዓቶች፣ ቀለበት እና ጥንድ የሸሚዝ ማያያዣዎችን ያካትታሉ።
ፓኪስታን ደም አፋሳሽ የሆነ የፖለቲካ አመጽ ታሪክ ያላት አገር ናት።
እንደ አውሮፓውያኑ 2007 በሕዝብ ስብሰባ ላይ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ቤናዚር ቡቶ መገደላቸው ይታወሳል።












