የፓኪስታን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር በሽብር ወንጀል ተከሰሱ

ካን ከስልጣናቸው ከተባረሩ በሏላ በአገሪቱ መንግስት ብሎም የመከላከያ ሰራዊት ላይ ትችቶችን ሲያደርሱ ቆይተዋል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

የፓኪስታን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ካሃን በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው ክስ ተመሰረተባቸው።

ካሃን ክስ የተመሠረተባቸው ፖሊስ የቅርብ አማካሪያቸውን ስቅይት እንደተፈጸመባቸው በመግለጽ ክስ ቅሬታ ካቀረቡ በኋላ ነው።

የቀድሞው መሪ የሚታሰሩ ከሆነ "እርምጃ እንወስዳለን" ያሉ ደጋፊዎቻቸው ከቤታቸው ደጃፍ መሰባሰባቸው በአገሪቱ ውጥረት አንግሷል።

በሚያዝያ ወር ከስልጣን ከተነሱ በኋላ ካሃን በመንግሥት እና በሃገሪቱ ጦር ላይ ከፍተኛ ትችት ሲሰነዝሩ ቆይተዋል።

ቀድሞ የክሪኬት ተጫዋች ካሃን የቅርብ ረዳት የነበሩ አንድ ግለሰብ አመጽ ማነሳሳት ክስ ተመስርቶባቸው በእስር ላይ ይገኛሉ።

ካሃን ቅዳሜ ዕለት ባደረጉት ንግግር የኢስላማባድ ፖሊስ አዛዥን እና አንዲት ዳኛ በፓርቲያቸው ባልደረባ ላይ እስር እና በደል ፈጽመዋል በሚል ኮንነዋቸዋል።

ሁለቱንም በቀጥታ በመጥቀስ "እናንተ ላይ እርምጃ ስለምንወስድ ተዘጋጁ" ሲሉ ተናግረዋል።  

ካሃን በመንግሥት አመራሮች ዝተዋል በሚል ባለስልጣናት የሃገሪቱን የፀረ-ሽብርተኝነት ድርጊት ጥሰዋል ሲሉ ከሰዋቸዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የምርመራው ዜና ከተሰማ በኋላ በመቶዎች የሚቆጠሩ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ደጋፊዎች ኢስላማባድ በሚገኘው የቀድሞው ፕሬዘዳንት ቤት ደጃፍ ላይ ተሰባስበዋል።  ፖሊስ የቀድሞውን መሪ ለማሰር የሚሞክር ከሆነ ዋና ከተማዋን "እንደሚቆጣጠሩም" ዝተዋል።

በስፍራው የተገኙ ፖሊሶች የቀድሞውን መሪ በቁጥጥር ስር ለማዋል ሳይሆን ሕግና ስርዓትን ለማስጠበቅ መገኘታቸውን ተናግረዋል።

ካሃን ባለፈው ሚያዝያ ወር የአገሪቱ ፓርላማ በሰጠው የመተማመኛ ድምጽ ከስልጣን መባረራቸው ይታወሳል።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር በሃገሪቱ እየተዘዋወሩ አዲስ ምርጫ እንዲካሄድ የጠየቁ ሲሆን የአገሪቱ መንግሥትን እና ሠራዊቱን ክፉኛ በመተቸትም ተከታታይ ንግግሮችን አድርገዋል።

የፓኪስታን የመገናኛ ብዙሃን ተቆጣጣሪ ቅዳሜ ዕለት ባወጣው መግለጫ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የካሃንን ንግግር በቀጥታ ካሰራጩ እንደሚታገዱ አስጠንቅቋል። ካሃንንም በመንግሥት ተቋማት ላይ የጥላቻ ንግግር ይሰነዝራሉ በሚልም ከሷቸዋል።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መንግሥት ሳንሱር ሊያደርገኝ እየሞከረ ነው ይላሉ። እሑድ ዕለት ደግሞ በራዋልፒንዲ ከተማ በተካሄደ የፖለቲካ ስብሰባ ላይ እገዳውን ተችተዋል ።

"ኢምራን ካሃን ምን ወንጀል ሰርቷል? ይህን የሌቦች ቡድን በፍጹም አልቀበልም" ሲሉ ለደጋፊዎቻቸው ተናግረዋል።

ካሃን በኋላም ሰዎች በቀጥታ እንዳያዳምጧቸው ለማድረግ መንግሥት ዩቲዩባቸውን ማገዱንም በንግግራቸው አጋማሽ ላይ አሳውቀዋል።

ኢምራን ካሃን በዚህ ዓመት መጀመሪያ ከስልጣን ቢባረሩም የብዙ የፓኪስታናዊያንን ድጋፍ ማግኘታቸውን ቀጥለዋል።

ባለፈው ወር ፓርቲያቸው ፒቲአይ በፑንጃብ ግዛት ብዙዎችን ያስደነቀ ድል በማስመዝገብ የክልሉን ጉባኤ መቆጣጠር ችሏል።

ይህ ምርጫ ካሃን ያላቸውን ተቀባይነት የሚያሳይ ምልክት ነው ሲሉ ብዙዎች ሞግተዋል።

ካሃን እ.አ.አ. በ2018 ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የተመረጡ ሲሆን የስልጣን ዘመናቸውን ወደ ማገባደዱ ሲደርሱ ነበር በአገሪቱ ከፍተኛ ስልጣን እንዳለው ከሚነገርለት የፓኪስታን ጦር ጋር ውጥረት ውስጥ የገቡት።