ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካዊው ባለቤቱ ፍቺ ስለጠየቀችው ሰባት ቤተሰቡን ገደለ
የ42 ዓመቱ አሜሪካዊ ባለቤቱ ፍቺ ስለጠየቀችው ሰባት ቤተሰቦቹን ከገደለ በኋላ ራሱን ማጥፋቱን ፖሊስ ገለጸ።
በዩታ ግዛት በሚገኘው መኖሪያቸው ስምንቱ የቤተሰብ አባላት ሞተው ተገኝተዋል።
ግለሰቡ ባለቤቱን ጨምሮ አምስት ልጆቻቸውን እና የባለቤቱን እናት ገድሏል።
ማይክል ሀይት የተባለው የኢንሹራንስ ሽያጭ ሠራተኛ የ40 ዓመቷ ባለቤቱ ታውሻ እና የ78 ዓመት እናቷ ጌይል ኧርልን ከገደለ በኋላ አምስት ልጆቻቸውን ገድሎ ራሱን አጥፍቷል።
ከአምስቱ ልጆቻቸው ሴቶቹ 7፣ 12 እና 17 ዓመታቸው ሲሆን ወንዶቹ ደግሞ 4 እና 7 ዓመታቸው ነው።
ይኖሩበት የነበረው ኢኖክ ሲቲ አስተዳዳሪ ሮብ ዶትሰን እንዳሉት፣ አስክሬናቸው የተገኘው ባለቤትየው ይዛ በነበረው ቀጠሮ ሳትገኝ በመቅረቷ ጥቆማ ለፖሊስ ከተሰጠ በኋላ ነው።
ፖሊስ ቤታቸውን ሲፈትሽ የቤተሰቡ አስክሬን ተገኝቷል። ሁሉም የሞቱት በተተኮሰባቸው ጥይት እንደሆነም ተገልጿል።
ባለቤትየው የፍቺ ጥያቄ ያቀረበችው ታኅሣሥ ላይ ነበር።
የቤተሰቡ የቅርብ ሰው የሆነችው ቲና ብራውን “ታውሻ እጅግ ቀና እና ደግ ሰው ነበረች። ስለማንም ክፉ አትናገርም ነበር። ሰዎችን ደከመኝ ሳትል አገልግላለች። ልብሷን አውልቃ ለሰው የምትሰጥ ሰው ነበረች” ብላለች።
የከተማው ከንቲባ ጄፍሪ ቼስትነት ስለ ክስተቱ አስተያየት ሲሰጡ እንባ እየተናነቃቸው ነበር።
“በከተማችን እንዲህ ያለ ነገር እምብዛም አልሰማንም። ትንሹ ልጃቸው ከልጆቼ ጋር ጊቢ ውስጥ ይጫወት ነበር” ብለዋል።
የልጆቹ ትምህርት ቤቶችም ሐዘናቸውን ገልጸዋል።
የዩታ አገረ ገዢ ስፔንሰር ኮክስ “በትርጉም አልባው ግድያ” ሳቢያ ጉዳት ውስጥ ለወደቁ ሁሉ ሐዘናቸውን ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና ቀዳማዊት እመቤት ጂል ባይደን “አሳዛኝ ግድያ” ባሉት ክስተት ሐዘናቸውን ገልጸዋል።
የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ ካሪን ጄንፒሬ “በሳንዲ ሁክ የደረሰውን አሰቃቂ ግድያ አሥረኛ ዓመት አስበን ወር ሳይሞላን ሌላ የጅምላ ግድያ ተፈጽሟል። አምስት ሕጻናትን ቀጥፏል” ብለዋል።