ሩሲያ ወደተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተቃጡ በርካታ የድሮን ጥቃቶችን መክቻለሁ አለች

ታትሟል

የሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር ወደ ስምንት የሀገሪቱ ክፍሎች የተቃጡ በርካታ የድሮን ጥቃቶችን ማክሸፉን አስታወቀ።

ከተሰነዘሩት ጥቃቶች ትልቁ የሚባለው በሩሲያዋ ክራስኖዳር የተከሰተው ሲሆን በሥፍራው የነበረ የነዳጅ ማጣሪያ ጉዳት ደርሶበታል።

ስላቭያንስክ-ኦን-ኩባን በተባለው የነዳጅ ማጣሪያ ላይ በተሰነዘረው ጥቃት የሞተ ሰው እንደሌለ የተዘገበ ሲሆን በጥቃቱ ምክንያት የተነሳው እሣትም በቁጥጥር ሥር ውሏል።

ሩሲያ ጠቅላላ ምርጫ እያካሄደች ሲሆን ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ምርጫውን እንደሚያሸንፉ ምንም ጥርጥር የለውም የሚሉ ዘገባዎች እየወጡ ነው።

ባለሥልጣናት እንዳሉት ወደ ነዳጅ ማጣሪያ 17 ድሮኖች ተተኩሰው ሁሉም ከጥቅም ውጭ ቢሆኑም አንድ ድሮን ሲወድቅ እሣት ፈጥሯል።

በጥቃቱ ወቅት አንድ ሰው በልብ ድካም ሳቢያ መሞቱ ተዘግቧል።

የአሁኑን ጨምሮ ባሳለፍነው ሳምንት ብቻ በሩሲያ ስድስት የነዳጅ ማጣሪያዎች ጥቃት ተሰንዝሮባቸዋል።

በተያያዘ ዜና የሞስኮው ከንቲባ ሰርጌይ ሶብያኒን በቴሌግራም ገፃቸው አራት ድሮኖች ወደ መዲናዋ እየበረሩ ሳለ ተመትተው ወድቀዋል ብለዋል።

የመከላከያ ሚኒስቴሩ ደግሞ አራት ድሮኖች በሞስኮው ሰሜናዊ አቅጣጫ ወደ ምትገኘው ያሮስላልቭል ግዛት እየበረሩ ሳለ መክሸፋቸውን አስታውቋል።

ከሰሜን ዩክሬን ጋር ድንበር በምትዋሰነው ቤልጎሮድ ግዛትም እንዲሁ ጥቃት እንደተሰነዘረባት የግዛቲቱ አስተዳዳሪ ገልጠዋል።

ቪያቼስላቭ ግላድኮቭ እንዳሉት አራት ድሮኖች ኦክትያብርስኪ ወደተሰኘው አካባቢ ፈንጂ ጥለው የአሌክትሪክ ኃይል እና የነዳጅ ማቅረቢያ መሥመርን መትተዋል። ነገር ግን ምንም ዓይነት ጉዳት ሰው ላይ አልደረሰም።

በካሉጋ፣ ኦርዮል፣ ሮስቶቭ እና ኩርስክ ግዛቶችም እንዲሁ የድሮን ጥቃቶች እንደተሰነዘሩ ተዘግቧል።

ቤልጎሮድ ግዛት ባለፉት ጥቂት ቀናት ብቻ ጥቃት ሲድርስባት ለሁለተኛ ጊዜ ነው።

ባለፈው ቅዳሜ በደረሰ የአውሮፕላን ጥቃት ሁለት ሰዎች ከተገደሉ በኋላ የሩሲያ ባለሥልጣናት ዩክሬንን ተጠያቂ አድርገዋል።

ጥቃቱን ተከትሎ ሱቆች እና ትምህርት ቤቶች ለደኅንነት ሲባል ተዘግተው ውለዋል።

የሩሲያ ባለሥልጣናት ጨምረው እንደገለጡት ከዩክሬን በተሰነዘሩ የድሮን ጥቃቶች በምዕራባዊቷ ሳማራ ግዛት የሚገኙ ሁለት የነዳጅ ማከማቻዎች ተመትተዋል።

ፕሬዝደንት ፑቲን፤ ዩክሬን ለስድስተኛ ጊዜ እንዳይመረጡ ለማደናቀፍ እየሞከረች ነው ሲሉ ወቅሰዋል።

ፑቲን ለስድስተኛ ጊዜ እንደሚመረጡ እርግጠኛ የሆኑት ይህ ነው የሚባል ተቀናቃኝ ስሌላቸው ነው የሚሉ ተቺዎች ምርጫው በምንም መሥፈርት ነፃ እና ፍትሐዊ አይደለም ሲሉ ይወቅሳሉ።

እሑድ ዕለት የወጡ ዘገባዎች እንደሚጠቁሙት ሩሲያ፤ በዩክሬኗ የባሕር በር ከተማ ኦዴሳ የአየር ጥቃት እያደረሰች ነው። በከተማዋ ከጥቂት ቀናት በፊት በደረሰ የሚሳዔል ጥቃት 20 ሰዎች ሲገደሉ በርካቶች ቆስለዋል።

የደቡብ ዩክሬን ጦር ሠራዊት እንደሚለው 13 ኢራን ሰራሽ ሻሄድ ድሮኖች ተመትተው ወድቀዋል። በዚህ ጥቃት ምክንያት የተገደሉ ሰዎች ባይኖሩም ሁለት የግብርና ጣቢያዎች እና ሕንፃዎች መውደማቸው ተሰምቷል።