ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቻምፒየንስ ሊግ፡ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚሳተፉ የአርሰናል ተጫዋቾችና የጀርመኑን ኃያል የሚገጥመው ዩናይትድ
ዛሬ ምሽት በሚደረገው በመጀመሪያው ዙር የቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታ በርካታ የአርሰናል ተጫዋቾች የመጀመሪያ ፍልሚያቸውን ሲያደርጉ ‘ቀውስ’ ውስጥ የገባው ዩናትድም ከጀርመኑ ኃያል ክለብ ጋር ለመጋጠም ወደ ሙኒክ ያመራል።
ረቡዕ ምሽት 4 ሰዓት አርሰናል ከ6 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ግዜ ወደ ቻምፒዮንስ ሊግ ተመልሶ የኔዘርላንድሱን ክለብ ፒኤስቪ አይንድሆቨንን ይገጥማል።
በፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያ ተሰላፊ ከሆኑ እና በዛሬው ጨዋታ የጀመሪያ የቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታቸውን ከሚያደርጉ ተጫዋቾች መካከል ግብ ጠባቂው ራምስዴል፣ ተከላካዮቹ ገብርኤል ማጋሌሽ እና ቤን ዋይት፣ ደክላን ራይስ፣ ቡካዮ ሳካ እና ኤዲ ኒኪታህ ተጠቃሽ ናቸው።
ከተጫዋቾቹ በተጨማሪ አሰልጣኝ አርቴታ ዋና አሰልጣኝ ሆነው ቡድንን በቻምፒየንስ መድረክ ሲመራ የመጀመሪያው ይሆናል።
የሰሜን ለንደኑ ክለብ ለመጨረሻ ግዜ በቻምፒየንስ ሊግ ውድድር ሲሳተፍ የቡድን አባል ሆኖ አሁንም በክለቡ የሚገኘው ግብጻዊው ሞሐመድ ኤልኒኒ ብቻ ነው።
መድፈኞቹ ባለፈው የፕሪሚየር ሊግ የውድድር ዓመት ማንቸስተር ሲቲን በመከተል ሁለተኛ ሆነው ማጠናቀቃቸውን ተከትሎ የቻምፒየንስ ሊግ ተሳታፊነታቸውን አረጋግጠዋል።
የሰሜን ለንደኑ ክለብ በምድብ ለ ከሴቪያ፣ ፒኤስቪ እና ላንስ ጋር ተደላድሏል።
ቀውስ ውስጥ ያለው ዩናይትድ
በፕሪሚየር ሊጉ ጥሩ ጅማሮ ማድረግ የተሳነው ሌላኛው የእንግሊዝ ክለብ ማንቸስተር ዩናይትድ ወደ አውሮፓ መድረክ ዛሬ ምሽት ይመለሳል።
ዩናይትድ በፕሪሚየር ሊጉ ከአምስት ጨዋታዎች ሁለቱን ሲያሸንፍ በሦስቱ ተሸንፏል።
ቡድኑ በተለይ በመጨረሻው ጨዋታው በሜዳው እና በደጋፊው ፊት በብራይተን 3ለ1 መሸነፉን ተከትሎ ቀውስ ውስጥ ገብቷል።
ዘ ሰን የተሰኘው ጋዜጣ እንደዘገበው ከብራይተን ጨዋታ በኋላ አምበሉ ብሩኖ ፈርንንዴዝን ጨምሮ አራት ተጫዋቾች በመልበሻ ክፍል ውስጥ አምቧጋሮ ፈጥረው ነበር።
ዩናይትድ ዛሬ በተመሳሳይ ረቡዕ ምሽት 4 ሰዓት የጀርመኑን ኃያል የሚገጥም ሲሆን አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግ ከጨዋታው በፊት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በጉዳት ምክንያት እስካሁን ድረስ ምርጥ የሚሏቸውን 11 ቀዳሚ ምርጫዎቻቸውን ማሰለፍ አለመቻላቸውን ተናግረዋል።
ቴን ሃግ ከዋናው ቡድን ስብስብ 12 ተጫዋቾቻቸውን ትተው ወደ ጀርመን ተጉዘዋል።
እንደ አንቶኒ፣ ጄደን ሳንቾ፣ ራፋኤል ቫራን፣ ሃሪ ማጓየር ያሉ ተጫዋቾች የቻምፒየንስ ሊግ የመክፈቻ ጨዋታ ከሚያልፋቸው ተጫዋቾች መካከል ይገኙበታል።
ማንቸስተር ዩናይትድ ከባየርን፣ ኮፐንሃገን እና ከቱርኩ ጋላታሳራይ ጋር ተመድቧል።