የሰሜን ኮሪያ መረጃ ሰርሳሪዎች የኒውክሌር ምሥጢር ለመስረቅ እየሞከሩ ነው ሲሉ አሜሪካ እና ዩኬ አስጠነቀቁ

መረጃ ሰርሳሪዎች

የፎቶው ባለመብት, Bill Hinton

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የሰሜን ኮሪያ መረጃ ሰርሳሪዎች የኒውክሌር እና ወታደራዊ ምሥጢር ከመንግሥታት እና ከግል ተቋማት ለመስረቅ እየሞከሩ ነው ሲሉ አሜሪካ፣ ደቡብ ኮሪያ እና ዩናይትድ ኪንግደም አስጠነቀቁ።

አንድሪያል እና ኦኒክስ ስሊት የሚል መጢያ ያለው መርጃ ሰርሳሪ ቡድን የመከላከያ፣ አየር ኃይል፣ ኒውክሌርና ምኅንድስና ዘርፎች ላይ በማነጣጠር ምሥጢር ለማግኘት እየሞከሩ ነው ሲሉ ከሰዋል።

የፒዮንግያንግ መንግሥት ምሥጢሮቹን ለወታደራዊና የኒውክሌር ፕሮግራሞቹ ለማዋል እየሞከረ ነው ሲሉም አስታውቀዋል።

መረጃ ሰርሳሪ ቡድኑ ዩራንየም ከሚያብላሉ ማከማቻዎች፣ ከሰርጓጅ መርከቦች እና የባሕር ሥር መሣሪያዎች መረጃ ለማግኘት እየሞከረ እንደሆነና ዒላማ ያደረገውም አሜሪካን፣ ዩኬን፣ ደቡብ ኮሪያን፣ ጃፓንን፣ ሕንድንና ሌሎችም አገራትን እንደሆነ ተገልጿል።

የአሜሪካ መከላከያ ኃይል፣ ናሳና ሌሎች ወታደራዊ ተቋማት ዒላማ ተደርገዋል ተብሏል።

ማስጠንቀቂያው የወጣው በከፍተኛ ደረጃ መሆኑ ቡድኑ እያከናወነ ያለው ስለላና ምዝበራ ከፍተኛ ባለሥልጣኖችን ስጋት ውስጥ መክተቱን ይጠቁማል።

ቡድኑ ገንዘብ የሚያገኘው የአሜሪካ የጤና ተቋማት ላይ የበይነ መረብ ጥቃት በመሰንዘር እንደሆነ አሜሪካ አስታውቃለች።

የዩኬ ብሔራዊ መረጃ ደኅንነት ማዕከል ዳይሬክተር ፖል ቺቸስተር “ዛሬ ያጋለጥነው የሰሜን ኮሪያ ዓለም አቀፍ የስለላ መረብ የሚያሳየው የሰሜን ኮሪያ መንግሥት ወታደራዊና የኒውክሌር ግቡን ለመምታት የሚሄድበትን ርቀት ነው” ብለዋል።

“እነዚህን ጥንቃቄ የሚፈልጉ መረጃዎችና አእምሯዊ ንብረቶች መጠበቅ ምን ያህል ዋጋ እንዳለው ለመረጃ መረብ ባለሙያዎች ሊያስታውስ ይገባል” ሲሉም አክለዋል።

አንድሪያል የተባለው ቡድን የሰሜን ኮሪያ ስለላ ተቋም አካል እንደሆነም አስታውቀዋል።

አሜሪካ፣ ዩኬና ደቡብ ኮሪያ ያወጡት ማስጠንቀቂያ የሰሜን ኮሪያን መረጃ ሰርሳሪዎች እንዴት መከላከል እንደሚቻል ይጠቁማል።

መረጃ ሰርሳሪዎቹ ከሮቦቶች፣ ሰው ሠራሽ ክንዶችና 3ዲ ኅትመት መረጃ ለመስረቅ መሞከራቸው ተገልጿል።

በጉግል ክላውድ ዋና ተንታኝ ማይክል ባርንሀርት “ሰሜን ኮሪያ በዜጎች የዕለት ከዕለት ሕይወት ላይ የደቀነችው አደጋ ችላ ሊባል አይገባም” ብለዋል።

“ምዝበራ ለማካሄድ ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ ሆስፒታሎች ላይ ማነጣጠራቸው በስለላ መረጃ ማግኘት እስከቻሉ ድረስ ድርጊታቸው በሰዎች ሕይወት ላይ የሚያሳድረው ጫና ግድ እንደማይሰጣቸው ይጠቁማል” ሲሉ አክለዋል።

ባለፉት ዓመታትም ተመሳሳይ ማስጠንቀቂያዎች ሲሰጡ ነበር።

ከፍተኛ የተባሉ የመረጃ ምዝበራዎች ከጀርባ ሰሜን ኮሪያ እንዳለች ሲገለጽ ቆይቷል።

የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ሲገደሉ የሚያሳይ ፊልም መሠራቱን ተከትሎ በ2014 በሶኒ ፒክቸርስ ላይ የደረሰው የመረጃ ጥቃት ይታወሳል።

ሰሜን ኮሪያ ያሰማራችው ላዛረስ ግሩፕ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዶላሮችን መዝብሯል።