ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ወደ ጣሊያን ከተሻገሩ ስደተኞች መሐል በጀልባ ውስጥ የተወለደ ጨቅላ ሞቶ ተገኘ
ጣሊያን ላምባዱሳ ደሴት ከደረሱ ስደተኞች መሐል ጀልባ ውስጥ በጉዞ ላይ ሳለ እንደተወለደ የተገመተ ጨቅላ ሞቶ መገኘቱን የጣሊያን ባለሥልጣናት ገለጹ።
አንሳ ዜና አገልግሎት እንደዘገበው ጨቅላው ምናልባትም እናት ከሰሜን አፍሪካ ወደ ጣሊያን የጀልባ ጉዞ ስታደርግ የተወለደ ሳይሆን አይቀርም።
ባለፉት ሦስት ቀናት ብቻ ሦስት ሺህ ስደተኞች ወደ ጣሊያን በጀልባ ተጉዘው ገብተዋል።
የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ዛሬ እሑድ ላምባዱሳ ደሴትን ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል። ኅብረቱ ጣሊያንን በሚያግዝበት ሁኔታም ይመክራሉ።
የጣሊያን ጋዜጦች እናቲቱ ምጥ ጀልባ ውስጥ ጀምሯት እንደተፋፋመባትና አብረዋት በነበሩ ስደተኞች እርዳታ እንደወለደች ምንጭ ጠቅሰው ጽፈዋል።
የጨቅላው ሬሳ በነጭ የሬሳ ሳጥን ተደርጎ በላምባዱሳ ኢምብሪያኮላ ቀበሌ መቀበሩንም ዘግበዋል።
በተገባደደው ሳምንት መባቻ በተመሳሳይ ስደተኞችን ከጫነች ጀልባ የ5 ወር ሕጻን መሞቱ ይታወሳል። ይህ የሆነው ጀልባዋ ላምባዱሳ ጠረፍ እየደረሰች በነበረበት ወቅት እርዳታ ሰጪዎች ለስደተኞቹ እገዛ በማድረግ ላይ ሳሉ ነበር።
የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጂዮርጂያ ሜሎኒ አገራቸው ከአፍሪካ በሚነሱ ስደተኞች ምክንያት ከባድ ጫና ውስጥ መውደቋን ጠቅሰዋል።
ሜሎኒ የስደተኛ ጀልባዎች ሜዲትራኒያንን ፈጽሞ እንዳያቋርጡ የአውሮፓ ኅብረት የባሕር ኃይል እንዲያቆም ይፈልጋሉ።
የጣሊያን ቀይ መስቀል ማኅበር በስደተⶉች መቀበያ ለ2500 ሰዎች ድጋፍ እያደረገ እንደሆነ ገልጧል።
በጎ ፈቃደኞች ለስደተኞች ምግብ እያቀረቡና ከሲሲሊ ወደ ሌሎች መጠለያዎች እያጓጓዙ ይገኛሉ።
በያዝነው የፈረንጆች ዓመት ብቻ ከሰሜን አፍሪካ 120ሺህ ስደተኞች በጀልባ ወደ ጣሊያን ገብተዋል። ይህ አሐዝ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በእጥፍ ጨምሯል።
ሜሎኒ የአውሮፓ ኅብረት ፕሬዝዳንት ኦርሶሎ ቫን ዶ ሌየን የሁኔታውን ስፋትና ጥልቀት በአካል መጥተው እንዲመለከቱ ነው የጋበዝኳቸው ብለዋል።
ሜሎኒ በተጨማሪ የአውሮፓ ኅብረት ከቱኒዚያ ጋር አሳሪ ስምምነት እንዲፈጽም ይፈልጋሉ።
ቱኒዚያ አሁን ከአፍሪካ የሚነሱ ስደተኞች ጉዞ የሚጀምሩባት ዋንኛ አገር ሆናለች።
በየጊዜው በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የመጣው የስደተኞች ወደ ላምባዱሳ ደሴት መጉረፍ የደሴቲቱን ነዋሪዎች ያስቆጣ ሲሆን አደባባይ ሰልፍ ለመውጣትም ተገደዋል።
ለስደተኞች ማቆያ የሚሆን ጊዝያዊ መጠለያ በደሴቲቱ ሊገነባ መታሰቡንም በይፋ ተቃውመዋል።
“ሁለት ልጆች አሉኝ፤ በፊት ስለስደተኞች መምጣት ብዙም ግድ አልነበረኝም፤ አሁን ግን ደኅንነት አይሰማኝም ፤ለዚህ ነው ሰልፍ የወጣሁት’’ ብሏል አንድ የደሴቲቱ ነዋሪ ለሮይተርስ።
‘’የላምባዱሳ ነዋሪዎች አሁን ሰልችቶናል። መልእክታችን ለአውሮፓ ኅብረትም ለጣሊያን መንግሥትም ነው፤ በቃ’’ ይላል ትናንት አደባባይ የወጣ ሌላ የላምፓዱሳ ነዋሪ።