ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኢራናዊቷ ታዳጊ ተቃዋሚ አስከሬን መሰረቁን ምንጮች ገለጹ
የኢራን የጸጥታ ኃይሎች የ16 ዓመቷን ታዳጊ ተቃዋሚ አስከሬን ሰርቀው በአንድ መንደር ውስጥ በድብቅ እንደቀበሯት ለቤተሰቧ ቅርብ የሆኑ ምንጮች ለቢቢሲ ፋርስ ተናግረዋል።
የታዳጊዋ ኒካ ሻክራሚ ቤተሰብ ሰኞ እለት ለመቅበር አቅደው የነበረ ቢሆንም አስከሬኗ ተሰርቆ 40 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኝ መንደር እንደተቀበረች ምንጮች ተናግረዋል።
ኒካ ቴህራን ውስጥ የነበረውን ተቃውሞ ከተካፈለች በኋላ ለአስር ቀናት ያህል መጥፋቷ ተገልጿል።
ኒካ ከመጥፋቷ በፊት በመጨረሻም ለጓደኛዋ ባስተላለፈችው መልዕክት የጸጥታ ኃይሎች እያባረሯት መሆኑን አክስቷ ለቢቢሲ ፋርስ ተናግረዋል።
ከነዚህም ቀናት መጥፋት በኋላ አስከሬኗ በመዲናይቱ በሚገኝ የአስከሬን ማቆያ ክፍል ውስጥ ተገኝቷል።
“አስከሬኗን ለመለየት በሄድንበት ወቅት ፊቷን ለጥቂት ሰኮንዶች ያህል እንድንመለከት እንጂ ሙሉ ሰውነቷን እንድናይ አልፈቀዱልንም” በማለት የኒካ አክስት አታሽ ሻካራሚ ተናግረል።
የኒካ ቤተሰቦች በባለፈው ሳምንት እሁድ አስከሬኗን ወደ አገሪቱ ምዕራባዊ ክፍል ወደሆነው የአባቷ ትውልድ ከተማ ሆራማባድ ወስደውት ነበር።
ቤተሰቦቿ በኮራማባድ የኃዘን ስነ ስርዓት እንዳያደርጉ ከመከልከል በተጨማሪ የጸጥታ ኃይሎች የኒካን አስከሬን ሰርቀው ቬይሲያን በተሰኘች መንደር እንደቀበሯት አንድ ምንጭ ተናግረዋል።
በመቶዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች በኮራማባድ መካነ መቃብር ተሰብስበው መንግሥትን በመቃወም መፈክሮችን ሲያሰሙ የነበረ ሲሆን ከዚህም ውስጥ “ሞት ለአምባገኑ” ሲሉም ነበር።
በማህበራዊ ሚዲያ ገጾቿ ላይ ስለ ኒካ የለጠፈችው አታሽ እሁድ ዕለት የጸጥታ ኃይሎች ቤቷ ሄደው በቁጥጥር ስር መዋሏን ምንጮች ተናግረዋል።
የጸጥታ ኃይሎች በተቃውሞ ሰልፉ ላይ ከቤተሰቦቿ ውስጥ አንድም ሰው ከተካፈለ አታሽን ለመግደል እንዳስፈራሯት ምንጮች አክለዋል።
ባለስልጣናቱ የተጎጂ ቤተሰቦችን ዝም ለማሰኘት የተቃዋሚዎችን አስከሬን እንደ መደራደሪያ የመጠቀም ልምድ አላቸው።