ፌደራል ፖሊስ "60" ስደተኞችን ለሞት ዳርገዋል የተባሉ 17 ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Federal Police
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ "ከ60 በላይ" ለሚሆኑ ስደተኞች ሞት እና "ለበርካታ ሴቶች" መደፈር ተጠያቂ ናቸው የተባሉ 17 "አደገኛ የሰዎች አዘዋዋሪዎች" በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አስታወቀ።
የመን ውስጥ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ "ከፍተኛ ኢሰብአዊ ድርጊቶች" ይፈጽሙ ነበር የተባሉት እነዚህ ተጠርጣሪዎች፤ "ከተጎጂዎች ከ1 ቢሊየን ብር በላይ" መሰብሰባቸውንም ገልጿል።
ፌደራል ፖሊስ ዛሬ ማክሰኞ ሐምሌ 14/2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ይህ የሰዎች አዘዋዋሪ ቡድን የሚመራው "መሐመድ ጣሂር አደን" ወይም "ወርዲ" በተባለ ግለሰብ ነው። የዚህን ተጠርጣሪ ጨምሮ በቁጥጥር ስር የዋሉት 17 ወንዶች ፎቶግራፍ ይፋ አድርጓል።
ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር ዋሉት "ከፍትሕ ሚኒስቴር፣ ከብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት እንዲሁም ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር" በተደገ ጠንካራ ክትትል እና ምርመራ እንደሆነ ገልጿል።
የፌደራል ፖሊስ መግለጫ፤ ግለሰቦቹ መቼ እና የት በቁጥጥር ስር እንደዋሉ አልጠቀሰም።
የፌደራል ፖሊስ ሚዲያ እና ኮሚዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ ጄይላን አብዲ፣ ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር የዋሉበት "ኦፕሬሽን ከሰሞኑ ለ15 ቀናት መካሄዱን" ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ግለሰቦቹ በአዲስ አበባ ከተማ እና ሐረሪ ክልል ጨምሮ ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች እንደተያዙም አክለዋል።
ፌደራል ፖሊስ ባወጣው መግለጫ፤ ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ "በሰው እና በሰነድ ማስረጃ" የተገደፈ የምርመራ መዝገብ ተደራጅቶ ለፍትሕ ሚኒስቴር መተላለፉን አስታውቋል።
"አደገኛ ሕገ-ወጥ አዘዋዋሪ" ተብሎ በተገለጸው መሐመድ ጣሂር አደን የሚመራው ይህ "የተደራጀ የወንጀል ቡድን" ሰዎችን በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ሲልክ እንደነበር መግለጫው ያስረዳል። ስደተኖቹን ሲያዘዋውሩ የነበረው ከኢትዮጵያ ምሥራቃዊ ክፍል በመነሳት በጂቡቲ እና በየመን በኩል በማቋረጥ እንደሆነ ተገልጿል።
ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች "በደላሎች አማካኝነት" ስደተኞችን ሲመለምሉ እንደነበረም ጠቅሷል። "ተጠርጣሪዎቹ የሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር መረብ በመዘርጋት፣ ተጎጂዎቹ በየመን በኩል ወደ ሳዑዲ አረቢያ ገብተው የተሻለ ኑሮ እንደሚኖሩ ሐሰተኛ ተስፋ በመስጠትና በማሳመን [ሲልኩ] ቆይተዋል" ብሏል።
እንደ ፌደራል ፖሊስ ገለጻ፤ ኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች ድንበር ከተሻገሩ በኋላ ግን "ለከፍተኛ ኢሰብአዊ ድርጊቶች" ተጋልጠዋል። ስደተኞቹ "ወደ የመን ተወስደው የመን ውስጥ በሚገኙ ለዚሁ ዓላማ በተዘጋጁ መጋዘኖች ታጉረው ከፍተኛ ኢሰብአዊ ድርጊቶች ይፈጸሙባቸው ነበር" ብሏል።
በእነዚህ መጋዘኖች ውስጥ ከተያዙት ስደተኞች ቤተሰቦች "ከፍተኛ ገንዘብ" እንደተጠየቀ መግለጫው ያስረዳል። ተጎጂዎቹን "እየደበደቡ እንዲሁም እያሰቃዩ ቪዲዮ በመቅረጽ" ገንዘቡን መክፈል ወዳልቻሉ ቤተሰቦች ይልኩ እንደነበር ማረጋገጡንም ፌደራል ፖሊስ ገልጿል።
በዚህ ተግባር "ከ1 ቢሊየን ብር በላይ በሕገ-ወጥ መንገድ መቀበላቸውን" እንዲሁም "ከ40,000 በላይ ሰዎችን በሕገ-ወጥ መንገድ ማዘዋወራቸውን" አስታውቋል።
"ከ60 ሰዎች በላይ ለህልፈተ ሕይወት መዳረጋቸው እንዲሁም በርካታ ሴቶች መደፈራቸው በምርመራ ተደርሶባቸዋል" ሲልም ተጠርጣሪዎቹ ለስደተኞች ሞት ተጠያቂ መሆናቸውን አመልክቷል። እነዚህን ድርጊቶች በተመለከተም ፖሊስ "ከሳዑዲ አረቢያ እና ከኢትዮጵያ የበርካታ ሰዎች" ምስክርነትን በቪዲዮ መቀበሉንም አክሏል።
ግለሰቦቹ ባገኙት ገንዘብ "በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር ቋሚ እና ተንቀሳቃሽ ንብረት ማፍራታቸውን" እንደደረሰበት የገለጸው ፌደራል ፖሊስ፤ "በስማቸው የነበረ ቤት፣ ተሽከርካሪ እና ገንዘብ እንዲታገድ" መደረጉን በመግለጫው አስፍሯል።
ተጠርጣሪዎቹ ላይ የተደረገው በሰው የመነገድ፣ በሕገወጥ ሀዋላ እንዲሁም በሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ወንጀሎች ምርመራ ተጠናቆ ጉዳዩ ወደ ፍትሕ ሚኒስቴር መላኩ አስታውቋል።
የፌደራል የፍትሕ አካላት ካለፉት ወራት ወዲህ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ በሚደረግ ከፍተኛ የሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ የተሰማሩ ተጠርጣሪዎች ላይ የተወሰዱ እርምጃዎችን በተከታታይ ይፋ አድርገዋል።
ባለፈው ጥር በሕገ ወጥ መንገድ ከኢትዮጵያ ያስወጧቸውን ስደተኞች ሊቢያ ውስጥ አግተው "እጅግ አሰቃቂ" ድርጊት ፈጽመዋል እንዲሁም ገንዘብ ተቀብለዋል የተባሉ 28 ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ መመሥረቱን የፌደራል ዐቃቤ ሕግ አስታውቆ ነበር።
በእነዚህ ተከሳሾች ከተዘዋወሩት ስደተኞች ውስጥ የሁለቱ ሕይወት እንዳለፈ እና 15 ሰዎች "የደረሱበት እንዳልታወቀም" ተገልጿል።
መጋቢት ላይ ደግሞ "በዓለም አቀፍ ደረጃ ይፈለግ የነበረ አደገኛ ሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ" በሚል የተገለጸው ይትባረክ ዳዊት (ክብሮም) እና ዘጠኝ ግብረ አበሮቹ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፌደራል ፖሊስ ማስታወቁ ይታወሳል።
ፌደራል ፖሊስ፤ በትግራይ ክልል ሽሬ ከተማ በቁጥጥር ስር የዋለው ይትባረክ ዳዊት "ከ100 በላይ ሰዎችን ለሞት የዳረገ እና ከ50 በላይ ሴቶች እንዲደፈሩ ያደረገ" መሆኑን በመጥቀስ ወንጅሏል።















