የየመን ሁቲዎች ሳዑዲ አረቢያ ላይ "የባሕር እንቅስቃሴ ማዕቀብ" መጣላቸውን አስታወቁ

መሣሪያ የያዙ ታጣቂዎች

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, ማዕቀቡ ሳዑዲ አረቢያ በየመን ወደቦችን እና አየር ማረፊያዎችን በመዝጋቷ የተሰጠ ምላሽ እንደሆነ ሁቲዎች ገልጸዋል
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በቀይ ባሕር ላይ የሚንቀሳቀሱት የየመን ሁቲዎች ሳዑዲ አረቢያ ላይ የባሕር እንቅስቃሴ እገዳ መጣሉን አስታወቁ።

በኢራን የሚደገፈው ታጣቂ ቡድን ቃል አቀባይ፣ ማዕቀቡ በአስቸኳይ ተግባራዊ መሆን እንደሚጀመር ገልጸዋል። ማዕቀቡ ሳዑዲ ሁቲ በሚቆጣጠራቸው የሰሜን ምዕራብ የመን ወደቦችን እና አየር ማረፊያዎችን በመዝጋቷ የተወሰደ የበቀል እርምጃ እንደሆነ ተናግረዋል።

ሰኞ ዕለት የሁቲ ጦር ቃል አቀባይ ያህያ ሳሬ፣ ሳዑዲ አረቢያ ለ12 ዓመታት ያህል በምንወዳቸው ሕዝቦች ላይ "ፍትሓዊ ያልሆነ እና ጨቋኝ ከበባ" ፈፅማለች፤ ሃብቶቻችንን ዘርፋለች እንዲሁም ወደቦቻችንን እና አየር ማረፊያዎቻችንን በመዝጋት ሁሉን አቀፍ እገዳ ጥላለች ሲሉ ከስሰዋል።

ለዚህም ምላሽ ለመስጠት "በሳዑዲ ወንጀለኛ ጠላት ላይ የባሕር ማዕቀብ" መጣሉን ገልጸዋል። ቃል አቀባዩ ስለማዕቀቡ ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።

ሆኖም የሁቲ ሚዲያ ምክትል ኃላፊ ነስረዲን አሚር በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ እንዳሉት፣ የቀይ ባሕር ደቡባዊ መግቢያ ባብ አል ማንዳብ ወሽመጥ ለሳዑዲ አረቢያ መርከቦች ዝግ እየሆኑ ነው።

የታጣቂ ቡድኑን እርምጃ ተከትሎ የሳዑዲ አረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቀረቡበትን ክሶች አስተባብሎ፣ አገሪቷ መርከቦቿን ለመጠበቅ በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት አስፈላጊውን እርምጃ እንደምትወስድ ገልጿል።

ሳዑዲም ስለማዕቀቡ የሰጠችው ዝርዝር መረጃ የለም።

ቀይ ባሕር አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ጦርነት ከከፈቱ ወዲህ ከሳዑዲ አረቢያ ነዳጅ የሚጓጓዝበት ወሳኝ መስመር ነው።

የኢራን ጦርነት በባሕረ ሰላጤው የሆርሙዝ ወሽመጥ እንዲዘጋ ያደረገ ሲሆን ዓለም አቀፍ የነዳጅ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድሯል።

ሁቲዎች ሳዑዲ አረቢያ ላይ ማዕቀብ መጣላቸውን ያስታወቁት 2022 ላይ በታጣቂ ቡድኑ እና ሪያድ መካከል ከተደረሰው መደበኛ ያልሆነ የተኩስ አቁም ስምምነት ወዲህ ተዳፍኖ የቆየው ውጥረት ከተባባሰ ከሳምንት በኋላ ነው።

ሁቲዎች በሳዑዲ አረቢያ ደቡባዊ ምዕራብ በሚገኘው አብሃ አየር ማረፊያ ሚሳዔሎች መተኮሳቸውን ተናግረዋል።

ይህም ሳዑዲ በሰንዓ አየር ማረፊያ ላይ ፈፅመዋለች ላሉት የአየር ጥቃት ምላሽ እንደሆነ ገልጸዋል።

ጥቃቶቹ በሳዑዲ በሚደገፈው የየመን መንግሥት የተረጋገጡ ሲሆን እርምጃው ያለፈቃድ ሊያርፍ የነበረን የኢራን አውሮፕላን ለመከላከል የተወሰደ እንደሆነ አስረድቷል።

የመን እአአ በ2014 በተጀመረውና ሁቲዎች የሰንዓን መንግሥት ባስወገዱበት የእርስ በእርስ ጦርነት ከፍተኛ ቀውስ አጋጥሟታል።

ግጭቱ በ2015 በሳዑዲ የሚመራው ጥምረት በአገሪቷ መንግሥታዊ ሥርዓት ለመመለስ ጣልቃ ከገባ በኋላ ተባብሷል።

እንደ የተባበሩት መንግሥታት መረጃ በግጭቱ ከ15 ሺህ በላይ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ከ22 ሚሊዮን በላይ ሰዎች እርዳታ ፈላጊ የሆኑበት በዓለም ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ ቀውስ አስከትሏል።