የሊባኖስ ጦር እስራኤል ወደለቀቀችው መንደር እየገባ መሆኑን አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በአሜሪካ አሸማጋይነት ባለፈው ወር በተደረሰው ስምምነት አማካኝነት የእስራኤል ኃይሎች ከያዟቸው የሊባኖስ ግዛቶች በመውጣታቸውን፤ የሊባኖስ ወታደሮች በአገሪቱ ደቡባዊ ክፍል ወደሚገኘው "የሙከራ (ፓይለት) ዞን" መግባት መጀመራቸው ተገለጸ።
የሊባኖስ ጦር ባወጣው መግለጫ፣ ወታደራዊ አሃዶች በናባቲዬ አውራጃ በሚገኘው ዘውታር አል ጋርቢዬ መንደር መሰማራታቸውን አስታውቋል።
የእስራኤል ጦር በበኩሉ ይህ የሙከራ ዞን እቅድ ተግባራዊ መሆን መጀመሩን ገልጿል።
በዚህ እቅድ መሠረት እስራኤል ከሄዝቦላህ ጋር ግጭት በተደረገበት ወቅት ከተቆጣጠረቸው ግዛት ውስጥ ከተወሰነው ክፍል ወታደሮቿን ታስወጣለች። በኢራን የሚደገፈው ሄዝቦላህ ደግሞ ትጥቅ እንዲፈታ ይጠበቃል።
የወታደሮቹ ስምሪት የተሰማው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የሊባኖሱ መሪ ጆሴፍ አውን ዋሽንግተን ውስጥ ለሚያደርጉት ስብሰባ እየተዘጋጁ ባሉበት ወቅት ነው።
የሊባኖሱ ፕሬዝዳንት፤ ትራምፕ እስራኤል ከቀረው የደቡብ ሊባኖስ ክፍል እንድትወጣ ጫና እንዲያደርጉ ይወተውታሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የሊባኖስ ጦር ሄዝቦላህ የያዛቸውን አካባቢዎች ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ለሚያደርገው ጥረት እገዛ እንደሚጠይቁም ይታሰባል።
ሊባኖስ፤ እስራኤል እና አሜሪካ ከኢራን ጋር ወደሚያደርጉት ጦርነት ተጎትታ የገባችው ሄዝቦላህ የኢራን ጠቅላይ መሪ ላይ የተፈጸመውን ግድያ ለመበቀል ወደ እስራኤል ሮኬቶችን ከተኮሰ በኋላ ነው።
እስራኤል በመላው ሊባኖስን በመደብደብ እና በአገሪቱ ደቡባዊ ክፍል የሚገኝ ሰፊ ግዛትን በመውረር ምላሽ ሰጥታለች። መንደሮችንም አውድማለች።
ሊባኖስ ውስጥ በተፈጸሙት የእስራኤል ጥቃቶች 800 ህጻናት፣ ሴቶች እና የጤና ባለሙያዎችን ጨምሮ 4,300 ሰዎች መገደላቸውን የአገሪቱ ጤና ሚኒስትር አስታውቋል።
የእስራኤል ባለሥልጣናት በበኩላቸው 37 የእስራኤል ወታደሮች እና አራት ንጹኃን መገደላቸውን ተናግረዋል።











