ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ወደ አውሮፓ መግባት ለሚፈልጉ ሩሲያውያን የቪዛ ሕጉ ጠበቀ
የሩሲያ ዜጎች የአውሮፓ አገራት ቪዛ ለማግኘት የሚያደርጉት ማመልከቸ ረዥም፣ ውድ እና ከባድ እንዲሆንባቸው የሚያድርግ ሃሳብ በአውሮፓ ሕብረት ሊተዋወቅ ነው።
ይህ ማለት ወደ አውሮፓ ህብረት አገራት ለመግባት የሚፈልጉ ሩሲያውያን ረዘም ያለ የማመልከቻ ሂደት ይጠብቃቸዋል። የማመለከቻ ክፍያውም ከ34 ዶላር ወደ 79 ዶላር ከፍ ይላል ተብሏል።
የአውሮፓ ሕብረት ኮሚሽን ሞስኮ በዩክሬን ላይ የከፈተችው ጦርነት እስከሚያበቃ ድረስ ይህ ረዥም እና ውድ ማመልከቻ ሊቀጥል ይገባል ብሏል።
የዩክሬን ወረራ ከጀመረ ወዲህ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሩሲያውያን ወደ አውሮፓ ሕብረት አገራት ተጉዘዋል።
የአውሮፓ ሕብረት ኮሚሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ማርጋሪቲስ ሺናስ እንዳሉት ሞስኮ የአውሮፓ ሕብረት እና የሩሲያ የቪዛ ስምምነት የተመሰረተበትን “እምነት ሙሉ በሙሉ ንዳዋለች።"
በስምምነቱ መሠረት ሩሲያውያን ላለፉት 15 ዓመታት የተቀላጠፈ የአውሮፓ ሕብረት ቪዛ ሂደት ተጠቃሚ ነበሩ።
የአውሮፓ ሕብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌየን በትዊተር ገፃቸው ከሩሲያ ጋር “የተለመደው ዓይነት ትስስር ሊኖር ስለማይችል የቪዛ ስምምነቱ መቋረጥ አለበት” ሲሉ ጽፈዋል።
ይህ እርምጃ ባለፈው ሳምንት የአውሮፓ ሕብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከሞስኮ ጋር የነበረውን የቪዛ ስምምነት ለማቆም በመርህ ደረጃ የተስማሙበትን ውሳኔ ተከትሎ የመጣ ነው።
ዩክሬን እና አንዳንድ የአውሮፓ ሕብረት አባል ሃገራት ሩሲያውያን ቪዛ እንዳያገኙ ሙሉ ለሙሉ እንዲታገዱ ጥሪ ቢያቀርቡም እንደ ፈረንሳይ እና ጀርመን ያሉት ግን ሃሳቡን ተቃውመዋል።
ሩሲያን የሚያዋስኑ የአውሮፓ ሕብረት አባል አገራት የድንበር ቁጥጥር ሥራቸውን ማጠናከር ጀምረዋል።
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ባለፈው ሳምንት እንዳስታወቁት የአውሮፓ ሕብረት ውሳኔ የሩሲያውያን ተጓዦችን ሕይወት የበለጠ አስቸጋሪ ያደርገዋል ያሉ ሲሆን፤ ሃሳቡንም “አስቂኝ ውሳኔ" ሲሉ ገልጸውታል።
በቀረቡት ሃሳቦች መሠረት የሩሲያ ዜጎች ቪዛ ለማግኘት
- ቀድሞ ከነበረው 35 ዩሮ ክፍያ ወደ የ80 ዩሮ ክፍያ ይጨምርባቸዋል
- ረዘም ያለ የማመልከቻ ሂደት ይጠብቃቸዋል
- ከአንድ ጊዜ በላይ መግቢያ ቪዛ ላይ ገደቦች ይጣልባቸዋል
- ከፍተኛ ቁጥር ያለው የድጋፍ ሰነዶች ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል
በሌላ በኩል የአውሮፓ ሕብረት ኮሚሽን አባል አገራት በሞስኮ ቁጥጥር ስር በሚገኙ የዩክሬን አካባቢዎች ለተሰጡ የሩሲያ ፓስፖርቶችን ዕውቅና እንዳይሰጡ ሃሳብ ያቀርባል።
የአውሮፓ ሕብረት የአገር ውስጥ ጉዳይ ኮሚሽነር ኢልቫ ዮሃንሰን "ሩሲያውያን ወደ አውሮፓ ሕብረት በቀላሉ መግባት የለባቸውም። እንደ ቱሪስት ወደ አውሮፓ ሕብረት መሄድ ሰብዓዊ መብትም አይደለም" ብለዋል።