ፖሊስ ልጅ ያሬድን “ሕዝብን ለማጋጨት በማሴር” ጠርጥሮ እንዳሰረው አስታወቀ

ፌደራል ፖሊስ በመድረክ ስሙ ልጅ ያሬድ በመባል የሚታወቀው ግለሰብ “ሃይማኖትን በመሳደብ እና ሕዝብን ለማጋጨት በማሴር” ጠርጥሮ በቁጥጥር ሥር እንዳዋለው ለቢቢሲ ገለጸ።
ልጅ ያሬድ በሚለው ስሙ የሚታወቀው ያሬድ ዘላለም በቅርቡ በማኅበራዊ ሚዲያው በኩል ያደረገው ንግግር በርካቶችን አስቆጥቷል።
በኮሜዲ፣ በስዕል እና በቅርፃ ቅርፅ ስራዎች የሚታወቀው ያሬድ ዘላለም ከቀናት በፊት አጸያፊ ቃላትን በመጠቀም የኦርቶዶክስ ሃይማኖት አባቶችን፣ የእምነቱ ተከታዮችን እና የአምልኮ ቦታን በማንቋሸሽ ተሳድቧል።
ይህን ተከትሎም ፌደራል ፖሊስ ተጠርጣሪውን ከአዲስ አበባ ወጣ ብሎ ከሚገኘው አሸዋ ሜዳ ተብሎ ከሚጠራው የመኖሪያ አካባቢው ባሳለፍነው አርብ ነሐሴ 26/2015 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር እንዳዋለው የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ቃል አበቃይ ጄይላን አብዲ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ጄይላን አብዲ ተጠርጣሪው በአሁኑ ሰዓት በአዲስ አበባ ሜክሲኮ የፌደራል የወንጀል ምርመራ ቢሮ በቁጥጥር ሥር ውሎ ምርመራ እየተደረገበት እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ቃል አቀባዩ የልጅ ያሬድ ንግግር ወንጀል በመሆኑ ማንም ክስ ሳይመሰርትበት ፖሊስ ቀድሞ በቁጥጥር ሥር አውሎታል ብለዋል።
“ወንጀል በመሆኑ ቀድመን በቁጥጥር ሥር አውለነዋል። ጉዳዩ ሕዝብን ከሕዝብ፤ ሃይማኖትን ከሃይማኖት የሚያጋጭ፤ አንድ ብሔር የተጠላ እንዲሆን የሚያደርግ በመሆኑ በቁጥጥር ሥር ውሏል” ብለዋል።
ልጅ ያሬድ በቁጥጥር ሥር ከዋለ ከጥቂት ቀናት በኋላ ማለትም ትናንት ሰኞ ነሐሴ 29/2015 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ግለሰቡ ላይ ክስ እንዲመሰረት ለፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮ በጻፈችው ደብዳቤ ጠይቃለች።
ቤተከርስቲያኗ የግለሰቡ ድርጊት በኮምፒዩተር አዋጅ ቁጥር 958/2008 እንዲሁም የጥላቻ ንግግር እና ሐሰተኛ መረጃን ለመከላከል የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1185/12 በመተላለፍ የቤተ ክርስቲያኗን መልካም ስም የሚያጎድፍ፣ ሰዎችን ለአመጽ እና ለብጥብጥ የሚያነሳሳ ድርጊት በመፈጸሙ በወንጀል ሊጠየቅ ይገባል ብላለች።
ቤተክርስቲያኗ የልጅ ያሬድ ንግግር የቤተ ክርስቲያን የአምልኮ ስፍራን ያራከስ፤ የምዕመናኑን ስሜት የነካ እና የዋረድ ነው ያለች ሲሆን ፖሊስ ተገቢውን ምርመራ በተባባሪዎቹ ላይ ጭምር አድርጎ ክስ እንዲመሠረትባቸው በላከችው ደብዳቤ ጠይቃለች።
የፌደራል ፖሊስ ቃል አቀባይ ጄይላን አብዲ ተጠርጣሪው ዓርብ ዕለት በቁጥጥር ሥር ከዋለ በኋላ ፍርድ ቤት ቀርቦ እንደነበረ ቢገልጹም ተጠርጣሪው በየትኛው ችሎት እንደቀረበ እንዲሁም ችሎት ላይ ምን እንደተባለ በዝርዝር ከመናገር ተቆጥበዋል።
“ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ድንበር ሊኖረው ይገባል” ያሉት ጄይላን “ሕዝብን በሃይማኖት እና ብሔራ ማጋጨት ወንጀል ነው” ብለዋል።












