አሜሪካ በስለላ ጠርጥራ ያፈነዳችው የቻይና ፊኛ 60 ሜትር እርዝማኔ እንደነበረው አስታወቀች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በአሜሪካ ባህር ዳርቻ ላይ እየሰለለ ነው በሚል የፈነዳው የቻይና ፊኛ 60 ሜትር እርዝማኔ እንደነበረው ተገለጸ።
ፊኛው የአውሮፕላን ያህል ጭነት መሸከም እንደሚችል እንደሚሸከም የአሜሪካ ባለስልጣናት ተናግረዋል።
የአሜሪካ የመከላከያ ባለስልጣን የፊኛው መጠን እና ይዘቱ ከተገመገመም በኋላ መሬት ላይ እያለ እንዳይተኮስበት ውሳኔም እንደተላለፈም ሰኞ እለት በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።
“በሺዎች ወይም በመቶዎች ኪሎግራም የሚመዝኑ ትላልቅ ቁርጥራጮች ከሰማይ ሲዘንቡ በዓይነ ህሊናችሁ አስቡት” በማለት ጄኔራል ግሌን ቫንሄርክ ተናግረዋል።
አሜሪካ በአሁኑ ወቅት በደቡብ ካሮላይና የባህር ዳርቻ ላይ ቁርጥራጮችን ፍለጋ ላይ ተሰማርታለች።
አሜሪካ የስለላ ነው ብትልም ቻይና የአየር ሁኔታ መቆጣጠሪያ መሳሪያ እንደሆነ የገለጸችው ፊኛ ቁርጥራጮች አንድ ሺህ ሜትር ስፋት ካለው ቦታ እየተሰበሰበ ቢሆንም ከዚያም አልፎ በመጠነ ሰፊ ሁኔታ እንደተበተነ ይታመናል።
ፊኛውን ተኩሶ ለማውረድ በርካታ የአሜሪካ ተዋጊ ጄቶች ተሳታፈ ሆነዋል።
ፊኛው በአሜሪካ የአየር ክልል ለቀናት ከታየ በኋላም ነው በአየር ኃይሉ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ቅዳሜ ተመትቶ የወደቀው። የፈነዳው ፊኛም ቁርጥራጭ በአሜሪካ የባህር ጠረፍ አካባቢን ሸፍኖታል ተብሏል።
“ከባህር ወለል በላይ የተገኙ ቁርጥራጮችን መሰብሰብ ተችሏል ነገር ግን የአየር ሁኔታው ባለመፍቀዱ በባህር ውስጥ የወደቁ ቁርጥራጮችን መሰብሰብሰና መቆጣጠር አልተቻለም” ሲሉ የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ቃለ አቀባይ ጆን ኪርቢ ሰኞ እለት ተናግረዋል።
የአሜሪካ ሰራተኞች በሚቀጥሉት ቀናት በውቅያኖሱ ስርጥ የወደቁ ቁርጥራጮችን እንደሚመረምሩ ገልጸው ነገር ግን ገና ጅማሮ ላይ እንደሆነም አክለዋል።
ቁርጥራጮቹን ለቻይና የመመለስ እቅደዝ እንደሌለ የገለጹት ባለስልጣናቱ የተገገኙ ቁርጥራጮች በስለላ ባለሙያዎች እንደሚተነተን አስረድተዋል።
ለዚህም ተግባር የሚያግዙ ልዩ መርከቦች ወደ አካባቢው የተሰማሩ መሆናቸውን ጄኔራል ቫን ሄርክ ተናግረዋል።
ፊኛው በመቶ ጫማዎች ቢረዝምም መሸከም የሚችለው ጭነት የአውሮፕላን ያህል ነው ብለዋል።
ከፊኛው የተረፉ ቁርጥራጮች አደገኛ የሆኑ ፈንጅዎችን ወይም ባትሪዎችን መያዛቸውን ለማረጋገጥ አሜሪካ በአሁኑ ወቅት ስራ መጀመሯንም ነው ጄኔራሉ ያስረዱት












