በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ መቃረባቸውን ባለሥልጣናት ገለጹ

ጋዛ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በእስራኤልና ሀማስ መካከል የተኩስ አቁም ለማድረግና ታጋቾችን ለመልቀቅ የሚደረገው ድርድር ወደ መጠናቀቁ መቃረቡን ለድርድሩ ቅርብ የሆኑት የፍልስጤም ባለሥልጣን ለቢቢሲ ገለጹ።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ስምምነቱ ፍሬ ለማፍራት "ከጫፍ ደርሷል" ብለዋል።

የእስራኤል ባለሥልጣንም ለሮይተርስ የዜና ወኪል ድርድሩ "ከፍ ያለ ደረጃ" ደርሷል ብለዋል።

ጆ ባይደን ከእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና ከሼኽ ታሚም ቢን ሐማድ አል-ታሕኒ ጋር ካታር ውስጥ መነጋገራቸው ተዘግቧል።

የፍልስጤም ባለሥልጣን ለቢቢሲ እንደገለጹት፣ ሀማስና የእስራኤል ባለሥልጣኖች ተገናኝተው እየተነጋገሩ ነው።

"ዝርዝር የድርድሩ ቴክኒካዊ ጉዳይ ጊዜ ወስዷል" ብለዋል።

ሀማስ ታጋቾቹን በስምምነቱ የመጀመሪያ ቀን እንደሚለቅ ተጠቁሟል። ከዚህ በኋላ እስራኤል ሕዝብ ከሚኖርባቸው አካባቢዎች ወታደሮቿን ታስወጣለች።

ከሰባት ቀናት በኋላ ሀማስ ተጨማሪ ታጋቾች ሲለቅ እስራኤል በደቡባዊ ጋዛ የተፈናቀሉ ነዋሪዎች በእግራቸው በዋና መንገድ አድርገው ወደ ሰሜናዊው አካባቢ እንዲመለሱ ትፈቅዳለች።

መኪና እና የእንሰሳት መጓጓዣዎች በሳላህ አል-ዲን ጎዳና የሚያልፉ ሲሆን፣ በካታርና ግብፅ ባለሙያዎች ፍተሻ ይደረግባቸዋል።

የእስራኤል ጦር ፊላደልፊ ኮሪደር በተባለው አካባቢ 800 ሜትር ላይ ከወታደር ነጻ አካባቢ ይዞ ለ42 ቀናት እንደሚቆይ በስምምነቱ ተካቷል።

እስራኤል 1,000 ፍልስጤማውያን እስረኞችን የምትለቅ ይሆናል። ከእስረኞቹ መካከል ወደ 190 የሚሆኑት 15 ዓመትና ከዚያ በላይ የተፈረደባቸው ናቸው።

ከዚያም ሀማስ በምላሹ 34 ታጋቾችን ይለቃል።

የተኩስ አቁም ከተተገበረ ከ16 ቀናት በኋላ የስምምነቱ ሁለተኛና ሦስተኛ ክፍል ይቀጥላል።

እስራኤላዊ አሜሪካዊ ልጁ የታገተበት አባት "እስራኤል እሺ ብላለች ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። አሁን በጭንቀት ውስጥ ነው ያለነው" ብሏል።

የዋይት ሀውስ ብሔራዊ ደኅንነት ኃላፊ ጄክ ሴሌቪን ስምምነቱ የባይደን አስተዳደር የመጨረሻ ሳምንት በሆነው በያዝነው ሳምንት እንደሚተገበር ተናግረዋል።

ባይደን ከግብፅ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አል-ሲሲ ጋር እንደሚነጋገሩም ተናግረዋል።

የተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የመካከለኛው ምሥራቅ ልዑክ ስቲቭ ዊትኮፍም በዶሀ በድርድሩ ላይ ተገኝተዋል።

ትራምፕ ሥልጣን ከመያዛቸው ቀድሞ ታጋቾች ካልተለቀቁ "የገሀነም በሮች ይከፈታሉ" ሲሉ ማስፈራራታቸው ይታወሳል።

የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጊዲዮን ሳር ድርድሩ "ከዚህ ቀደም ከነበረው በተሻለ መንገድ እየሄደ ነው" ብለዋል።

የኔታንያሁ ፓርቲ ውስጥ የሚገኙ አሥር ቀኝ ዘመም አባላት የተኩስ አቁም ስምምነቱን ተቃውመው ለኔታንያሁ ደብዳቤ ጽፈዋል።