በኢየሩሳሌም ቅዱስ ስፍራ አይሁዶች ጸሎት እንዲያደርጉ የጠየቁት የእስራኤል ሚኒስትር ተቃውሞ ገጠማቸው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የቀኝ አክራሪው የእስራኤል ሚኒስትር በመቶዎች የሚቆጠሩ አይሁዳውያንን አስከትለው የይገባኛል ጥያቄ ወደሚነሳበት የኢየሩሳሌም ክፍል መግባታቸው ተቃውሞ ገጠመው።
ሚኒስትሩ የእስራኤል መንግሥት በስፍራው የአይሁድ ጸሎት እንዳይደረግ ለረዥም ጊዜ ጥሎት የቆየውን እገዳ ተቃውመውታል።
የብሔራዊ ደኅንነት ሚኒስትሩ ኢታማር ቤን-ጊቪር በአይሁዶች ቴምፕል ማውንት በመባል በሚታወቀው የአል-አቅሳ መስጊድ ግቢ ያደረጉት ጉብኝት ከፍልስጤም መሪዎች በተጨማሪ በአሜሪካ፣ በፈረንሳይ፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና በተለያዩ የአረብ አገራት ቀስቃሽ ነው በሚል ውግዘት አስተናግዷል።
ቤን-ጊቪር “የእኛ ፖሊሲ የአይሁድን ጸሎት እንዲከናወን ማስቻል ነው” ሲሉ ቪዲዮው ላይ ተደምጠዋል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ግን የሙስሊም አምልኮን ብቻ የሚፈቅደው አቋም እና ስምምነት ላይ ምንም ዓይነት ለውጥ እንዳልተደረገ አስረግጦ ተናግሯል።
ቦታው የሁለት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቤተመቅደሶች ቦታ ስለነበረ ለአይሁዶችም ቅዱስ ቦታ ተደርጎ ይወሰዳል። ነቢዩ መሐመድ ያረጉበት ቦታ ነው ብለው ለሚያምኑት ሙስሊሞች ደግሞ ሦስተኛው ቅዱስ ስፍራ ነው።
በምሥራቅ ኢየሩሳሌም የሚገኘው ስፍራ በ1967 በተደረገው የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ወቅት እስራኤል ከዮርዳኖስ የያዘቸው ነው። አሁን ባለው ሁኔታ ዮርዳኖስ የቦታ ጠባቂ በመሆን ታሪካዊ ሚናዋን እንድትቀጥል ሲፈቀድላት፣ እስራኤል በበኩሏ የፀጥታ ጥበቃውን ትቆጣጠራለች።
እስራኤል የምትወስዳቸውን እርምጃዎች እየተቃወሙ የነበሩ ፍልስጤማውያን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ አይሁዳውያን ጎብኚዎች በእስራኤል ፖሊስ ክልከላ ሳይደረግባቸው ሲጸልዩ ታይተዋል ሲሉ ቅሬታቸውን አቅርበዋል።
ማክሰኞ ዕለት በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በተለቀቁ ቪዲዮዎች ላይ በርካታ እስራኤላውያን ብሔራዊ መዝሙር ሲዘምሩ፤ አንዳንዶቹ የእስራኤልን ባንዲራ ይዘው ሲታዩ ሌሎች ደግሞ በቅዱስ ስፍራው ጫፍ ላይ ለጸሎት ሲሰግዱ ታይተዋል።
በእስራኤል ፖሊስ ታጅበው ግቢውን የጎበኙት ኢታማር ቤን-ጊቪር በእስራኤል “አስተዳደር እና ሉዓላዊነት” ላይ “ትልቅ ለውጥ” ታይቷል ብለዋል። “የእኛ ፖሊሲ የአይሁድ ጸሎትን ማስደረግ ማስቻል ነው” ሲሉ አክለዋል።
እስራኤል የጋዛ ሰርጥ “ጦርነትን ማሸነፍ አለባት” እና “ሐማስን ለማንበርከክም” የተኩስ አቁም እና የታጋቾችን የመልቀቅ ስምምነት ላይ መሳተፍ እንደሌለባት አክለው አስታውቀዋል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጽህፈት ቤት ክስተቱ “ከነበረበት ሁኔታ ያፈነገጠ ነው” ሲል ገልጿል።
“እስራኤል በቤተ መቅደሱ ተራራ ላይ ያላት ፖሊሲ አልተለወጠም። ይህ ነበረ ነው፤ ወደፊትም ይቀጥላል” ሲል አጽንኦት ሰጥቷል።
ቤን-ጊቪር መግለጫውን አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት “ሁሉንም ቦታዎች ለአይሁዶች የአምልኮ ነፃነት ማስቻል” የራሴ ፖሊሲ ነው ብለዋል።
“በቴምፕል ማውንት ወይም በእስራኤል ውስጥ በአይሁዶች ላይ የዘረኝነት መድልዎ ማድረግን የሚፈቅድ ሕግ የለም” ሲሉም አክለዋል።
የፍልስጤም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር “አክራሪ ሰፋሪዎች በተቀደሰው አል-አቅሳ መስጊድ ላይ የፈጸሙት ወረራ ያስከተለውን አደገኛ ጠብ አጫሪነት” ከፍተኛ ስጋት እንደፈጠረበት ገልጿል።
“ሚኒስቴሩ በተለያዩ እርከኖች የሚነሱ ጠብ አጫሪ እርምጃዎች ለመፍታት የፖለቲካ ጥረቱን እንደሚቀጥል በመግለጽ በግጭቱ መድረክ እና በቀጠናው ላይ የሚያደርሱትን አስከፊ መዘዝም ለማስጠንቀቅ ይወዳል” ሲል መግለጫው ጠቁሟል።
ቦታውን የሚያስተዳድረው የዮርዳኖስ ኢስላሚክ ኢንዶውመንት ዋቅፍ በበኩሉ ከሁለት ሺህ በላይ ቤተ እስራኤላውያን ወደ ግቢው መግባታቸውን እና በመላው ዓለም የሚገኙ ሙስሊሞች ቀደም ሲል የነበረው ሁኔታ እንዲቀጥል እንዲደግፉት ተማጽኗል።
የዮርዳኖስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ክስተቱ “የእስራኤል መንግሥት እና ጽንፈኛ አባላቱ ዓለም አቀፍ ሕጎችን እና የእስራኤልን ግዴታዎች እንደ ወራሪ ኃይል ለመጣስ ያላቸውን ቁርጠኝነት” የሚያንጸባርቅ ነው ብሏል።
ግብፅ እና ሳዑዲ አረቢያ ክስተቱ ዓለም አቀፍ ሕግን የጣሰ ነው ብለዋል። ቤን ጊቪር በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ለመድረስ የሚደረገውን ሙከራ ማደናቀፍ እየሞከሩ ነው ስትል ግብፅ ከሳለች።
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በሰጡት መግለጫ ደግሞ የቤን-ጊቪር ጉብኝት በኢየሩሳሌም የሚገኙ ቅዱሳን ስፍራዎችን በተመለከተ ያለው ታሪካዊ አሠራር አለመከበሩን ያሳየ ነው ብለዋል።
“እነዚህ ቀስቃሽ ድርጊቶች የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ፤ ሁሉም ታጋቾች እንዲፈቱ እና ለሰፋፊ ቀጣናዊ መረጋጋት ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር በሚደረጉ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ላይ ትኩረት ማድረግ በሚኖርበት ወሳኝ ወቅት መከሰቱ ውጥረቱን ያባብሳሉ” ሲሉ አክለዋል።
የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሚስተር ቤን ጊቪር ጉብኝቱን አውግዘው “ይህ አዲስ ቅስቀሳ ተቀባይነት የለውም” ብለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቃል አቀባይ ፋርሃን ሃቅ ክስተቱን “ጠቃሚ ያልሆነ እና ያልተገባ ስሜት ቀስቃሽ” ነው ሲሉ ገልጸው፤ “በቅዱስ ስፍራዎቹ ያለውን ሁኔታ ለመለወጥ የሚደረግን ማንኛውንም ጥረት እንቃወማለን” ብለዋል።












