ፕሪሚየር ሊጉ በአዳዲስ ሕጎች እና ቡድኖች ተመልሷል፤ ምን ለውጥ ይደረጋል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፕሪሚየር ሊጉ ተጀምሯል። ሲቲ ለአምስት ተከታታይ ጊዜ ዋንጫን ሊያነሳ፣ መድፈኞቹ የ20 ዓመት የዋንጫ ጥማታቸውን ሊያሳኩ፣ ዩናይትድ በ30 ዓመታት ታሪኩ ካሳየው ደካማ አቋም ተሻሽሎ ለመቅረብ እና አዳጊው ኢፕስዊች አቅማቸውን ሊያሳዩ የተቻላቸውን ያደርጋሉ።
ሊጉ ትናንት ምሽት ዩናይትድ እና ፉልሃም ባደረጉት ጨዋታ ተጀምሯል።
ዛሬ ደግሞ ሊቨርፑል ወደ ሊጉ ያደገውን ኢፕስዊች ያስተናግዳል። መደፈኞቹ ደግሞ በኢሚሬትስ ከዎልቭስ ይጫወታሉ። በነገው ተጠባቂ ጨዋታ ደግሞ ማንችስተር ሲቲዎች ወደ ቼልሲ ያቀናሉ።
ዘንድሮ በሊጉ አዲስ ለውጥ ይኖራል። ኳስ በእንጅ ሲነካ፣ የባከነ ጊዜን እና በቪዲዮ የተደገፈ ዳኝነት (ቫር) በተመለከተ የሕግ ለውጥ ተደርጓል።
አዳዲሶቹ ሕጎች ምንድን ናቸው?
በአዲሱ ቫር - የመሃል ዳኛን የሚረዳው የቪዲዮ ዳኛ (ቪዲዮ አሲስታንት ሬፈሪ) ጣልቃ መግባት የሚችለው የመሃል ዳኛው “ያለ አንዳች ጥርጣሬ ግልጽ የሆነ ስህተት ከሰሩ” ብቻ ነው።
ይህ ማለት ቫር ጣልቃ ሊገባባቸው የሚችልባቸው አጋጣሚዎች ይቀንሳሉ።
በጨዋታ ወቅት ‘ፕሪሚየር ሊግ ማች ሴንተር አካውንት’ የተባለው አዲስ የተከፈተው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ የቫር ውሳኔዎችን የተመለከቱ ማብራሪያዎችን ያብራራል።
ገጹ በጨዋታ ወቅት በቫር አማካይነት የተሰጡ ውሳኔዎችን በስታዲየም ስክሪኖች ሳይቀር ለደጋፊዎች ማብራሪያ ይሰጣል።
ቫር ጣልቃ የሚገባባቸው የዳኛ ውሳኔዎች መቀነሳቸው፤ የባከነ ደቂቃ ጭማሪን በከፍተኛ መጠን ይቀንሳል ተብሏል።
ከዚህ ቀደም በጎል ምክንያት የሚባክን ጊዜ ተሰልቶ የሚጨመረው፤ ኳስ ከመረብ ከተገናኘበት ጊዜ አንስቶ ጨዋታው ዳግም እስከሚጀመርበት ያለው ጊዜ ተሰልቶ ነበር።
አሁን ግን ለእያንዳንዱ ግብ ባክኗል ተብሎ የሚጨመረው ሰዓት 30 ሴኮንድ ብቻ ይሆናል።
ከዚህ ውጪ ከቆሙ ኳሶች በሚጀመር ጨዋታ ወቅት የተጋጣሚ ቡድንን ለመከለል የሚደረግ ጥረት ቅጣት ያስከትላል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ባለፈው ዓመት የአርሰናሉ ተከላካይ ቤን ዋይት ቡድኑ በተለይ የማዕዘን ምት ሲያገኝ የተጋጣሚ ግብ ጠባቂ ፊት በመቆም ግብ ጠባቂዎች ኳሱን እንዳያገኙ እንቅፋት ሲሆን ታይቶ ነበር።
ከዚህ ውጪ ኳስ በእጅ መንካትን በተመለከተ የነበረው ሕግ እንዲላላ ተደርጓል።
ተጫዋቾች በፍጹም ቅጣት ምት ሳጥን ውስጥ ሲከላከሉ ኳስ እጃቸውን እንዳይነካ እጃቸውን ወደ ኋላ ማድረግ እንደማይጠበቀባቸው በፕሪሚየር ሊጉ ተነግሯቸዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ኳስ በእጅ ተነክቶ ፍጹም ቅጣት ምት ቢያሰጥ እንኳ ተጫዋቹ ሆነ ብሎ ኳስ በእጅ እስካልነካ ድረስ ካርድ እንደማይመለከት ተገልጿል።
የዳኞች ስብስብ ኃላፊው ሃዋርድ ዌብ ኳስ በእጅ ተነክቷል በሚል ይሰጡ የነበሩ ከበድ ያሉ ቅጣቶች ቀንሰው እንመለከታለን ብለዋል።
ኳስ አቀባዮች ኳስ ማቀበል የሚችሉት ለግብ ጠባቂ ብቻ ይሆናል። ሌሎች ተጫዋቾች ግን ጨዋታ ለማስጀመር ኳስ ከሜዳ ጎን ይቀመጥላቸዋል።
ሌላኛው አዲስ ለውጥ በአንድ ጊዜ አምስት የአንድ ቡደን ተቀያሪ ተጫዋቾች በጋራ ማማሟቅ እንዲችሉ መፈቀዱ ነው። ከዚህ ቀደም ከሜዳ ጎን በአንድ ጊዜ ተቀይሮ ለመግባት ዝግጁ የሚያደርጉ ተጫዋቾች ቁጥር ሦስት ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የፕሪሚየር ሊጉ አዳዲስ ፊቶች
በዘንድሮ ፕሪሚየር ሊግ አዳዲስ አሠልጣኞችን እና በርከት ያሉ አዲስ ፈራሚ ተጫዋቾችን እንመለከታለን።
ዘንድሮ አዳዲስ አምስት አሠልጣኞችን እንመለከታለን።
የሊቨርፑል አርን ስሎት፣ የቼልሲው ኤንዞ ማሬስካ፣ የሳዝውሃምፕተን ራስል ማርቲን፣ የኢፕስዊች ኪይርና ማክኪን እንዲሁም የብራይተኑ ፋቢያን ሃርዜሌር በእንግሊዝ ትልቁ ሊግ የመጀመሪያ ጨዋታዎቻቸውን ዛሬ እና ነገ ያደርጋሉ።
ከአሠልጣኞች በተጨማሪ በርካታ አዳዲስ ተጫዋቾችን በአዲሱ የውድድር ዓመት እንመለከታለን።
ዩናይትድ ከሊል ያስመጣው ሌኒ ዮሮ፣ ከቦሎኛ ያስፈረመው አጥቂ ጆሹዋ ዜርስ እና ከሙኒክ የመጡት ተከላካዮቹ ማቲያስ ዲ ላይት እና ማዝራዊ በቡድኑ ላይ የሚያመጡት ለውጥ የሚታይ ይሆናል።
ሲቲ ብራዚላዊውን የክንፍ ተጫዋች ሳቪንሆ ያስፈረመ ሲሆን፣ መድፈኞቹ ደግሞ ከጣልያን ባስፈረሙት ሪካርዶ ካላፊኦሪ የተከላካይ መስመራቸውን አጠናክረዋል።
ብራይተን ደግሞ ከኒውካስትል ዩናይትድ ያስፈረመው ያንኩባ ሚንቴህ የሚያሳየው ብቃት ይጠበቃል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ለፕሪሚየር ሊጉ እንግዳ የሆነው ኢፕሲች
ዘንድሮ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ካደጉት ሦስት ክለቦች ሁለቱ በሊጉ ብዙ ልምድ ያላቸው ሌስተር ሲቲ እና ሳውዝሃፕተን ናቸው።
ኢፕስዊች ታዎን ግን ወደ ፕሪሚየር ሊጉ የሚመለሱት ከ22 የውድድር ዘመናት በኋላ ነው።
ኢፕስዊች ወደ ፕሪሚየር ሊጉ የሚመጣው በሊጉ ምንም ሊባል የሚችል ልምድ የሌላቸውን ተጫዋቾች እና አሠልጣኝ ይዞ ነው።
ክለቡ በታሪኩ ከፍተኛ የሆነ 20 ሚሊዮን ፓዎንድ በማውጣት የቼልሲውን ኦማሪ ሃቺሰን አስፈርሟል። ከሃቺሰን በተጨማሪ ክለቡ ከሲቲ፣ ከዌስት ሃም እና ከበርንሌ ተጫዋቾችን አስፈርሟል።
ዋንጫውን ማን ያነሳል?
ማን ሲቲ አራት ተከታታይ የውድድር ዘመኖችን በማሸነፍ ታሪክ ሰርቷል። ለአምስተኛ ጊዜ አሸንፎ ሌላ ታሪክ ይጽፍ ይሆን?
አርሰናል ዘንድሮም ሁለተኛ ሆኖ ሊያጠናቅቅ?
የሚኬል አርቴታው አርሰናል ባለፉት የሁለት የውድድር ዓመቶች ከሲቲ በመቀጠል ሁለተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል። ለአርሰናል ደጋፊዎች ተሰፋ የሚሰጠው ቡድኑ በየዓመቱ እየተሻሻለ መምጣቱ ነው።
የቀድሞውን አሠልጣኝ የርገን ክሎፕን የተኩት አርን ስሎት አስደናቂ ነገሮችን ማሳካት የሚችል ቡድን አላቸው።
ባለፉት አምስት የውድድር ዓመታት ከሲቲ ውጪ ዋንጫናውን ያነሳው ብቸኛው ቡድን ሊቨርፑል የዋንጫ ተፎካካሪ ሆኖ ሊቀርብ ይችላል።












