ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሶማሊያ ፕሬዚዳንት አዲስ ጠቅላይ ሚንስትር ሾሙ
የሶሚሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ አዲስ ጠቅላይ ሚንስትር ሾሙ።
የፕሬዝዳንቱ ፓርቲ አባል እና የህዝብ እንደራሴ የሆኑት ሐምዛ አብዲ ባሬ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱ ሹመት ተሰጥቷቸዋል።
ፕሬዝዳንቱ ምርጫውን ለማከናወን ጊዜ ወስደው መወሰናቸውን ገልጸው ባሬም ጥሩ ዕጩ ሆነው ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
ሹመቱን ተከትሎ አስተያየታቸውን የሰጡት አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር የሶማሊያን አንድነት በማስጠበቅ ሃገሪቱን የማዳን ተግባር ላይ እንደሚያተኩሩ አስረድተዋል።
ሐምዛ አብዲ ባሬ በሶማሊያ መንግሥት ውስጥ የተለያዩ የስልጣን እርከኖች ላይ ሠርተዋል። እአአ ከ2019 እስከ 20220 ድረስ የጁባላንድ የምርጫ ኮሚሽን ሊቀመንበር ባገለገሉበትም ወቅት ነው ስማቸው የገነነው።
እአአ ከ2014 እስከ 2015 የቤናዲር ክልል ርዕሰ መስተዳድር እና የሞቃዲሾ ከንቲባ ለሆኑት ሐሰን መሐመድ ሁሴን አማካሪ ሆነው አገልግለዋል።
የሕገ መንግሥት ጉዳዮችና የፌደራሊዝም ጉዳዮች ሚኒስቴር ከፍተኛ አማካሪ ሆነውም አገልግለዋል።
ከሠላሳ ቀናት በፊት ሶማሊያ ሐሰን ሼክ መሀመድን የሶማሊያ 11ኛው ፕሬዝዳንት አድርጋ መርጣለች። ለረዥም ጊዜ ዘግይቶ የተካሄደው ምርጫ በቀድሞው ፕሬዝዳንት መሐመድ አብዱላሂ ፋርማጆ እና በጠቅላይ ሚኒስትራቸው መሀመድ ሁሴን ሮብሌ መካከል አለመግባባት ፈጥሮ መቆየቱ ይታወሳል።
አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሹመታቸው በፓርላማው ከጸደቀ በኋላ መንግሥት ይመሰርታሉ ተብሎ ይጠበቃል።