የትራምፕ አስተዳደር ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ ሕገ ወጥ ስደተኞችን ማሰር ይጀምራል

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በሕገ ወጥ መንገድ የሚኖሩ ሰዎች ማሰር እና መመለስ እንደሚጀምር የፕሬዝደንቱ ውስጥ አዋቂ ምንጮች ለቢቢሲው የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ ተናገሩ።
የድንበር ጉዳይን እንዲቆጣጠሩ በትራምፕ የተመረጡት ቶም ሆማን ከማክሰኞ ጀምሮ ስደተኞችን የማባረር ሥር እንደሚጀምሩ ተጠቁሟል።
ቶም በርካታ ስደተኞች ካሉባት የቺካጎ ከተማ ሊጀምሩ እንደሚችሉ ምንጮቹ አሳውቀዋል።
ትራምፕ በአሜሪካ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ስደተኞች እንደሚያባርሩ ቃል የገቡ ሲሆን ሆማን ደግሞ ወንጀለኞች እና የወንበዴ ቡድን አባላት ቅድሚያ እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል።
ፎክስ ኒውስ ለተባለው የቴሌቪዥን ጣቢያ ቃለ-ምልልስ የሰጡት ቶም ሆማን በመላው ሀገሪቱ "ትልቅ አሰሳ" ይካሄዳል ብለዋል።
ሰውዬው ከዚህ ቀደም ቺካጎ "የመጀመሪያዋ" በርካታ ስደተኞች ተለቅመው የሚባረሩባት ከተማ መሆኗን ተናግረው ነበር።
የድንበር ጥበቃ ኃላፊው እንደሚሉት ስደተኞችን ከሀገር የማስወጣት ሥራው "ታቅዶበት" የሚደረግ እንጂ በመላ-ምት የሚሆን አይደለም።
"[ሠራተኞቻችን] ሲሄዱ ማንን እንደሚፈልጉ እንዲሁም የት እንደሚያገኛቸው ያውቃሉ" ሲሉ ያብራራሉ።
ቶም እንደሚሉት ሕገ ወጥ ስደተኞች በትራምፕ ዘመን መንግሥት የመጀመሪያው ሳምንት በሚደረጉ በረራዎች ከአሜሪካ እንዲባረሩ ይደረጋሉ።
አሜሪካን ሲቪል ሊቨርቲስ ዩኒየን የተባለው ድርጅት ስደተኞች ከአሜሪካ የማስወጣት ተግባርን ተቃውሞ ክስ ሊያደርግ እንደሚችል ይጠበቃል።
"ክስ እንደሚቀርብብን እርግጠኛ ነኝ። ግድ የለንም። እንከሰስ" ይላሉ ኃላፊው።
ሪፐብሊካኑ ትራምፕ በአውሮፓውያኑ 2017 ለመጀመሪያ ጊዜ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ሆነው ሲመረጡ ስደተኞችን በገፍ እንደሚያባርሩ ቃል ገብተው ነበር። ነገር ግን ከዲሞክራቱ ባራክ ኦባማ ሲነፃፀር ግማሽ ያህሉን ብቻ ነው ያባረሩት።
47ኛው የአሜሪካ ፕሬዝደንት የድንበር ጥበቃን በተለመከተ ያስቀመጡት ፖሊሲ በ55 በመቶ አሜሪካዊያን ድጋፍ እንዳገኘ ኒው ዮርክ ታይምስ እና ኢስፖስ የሠሩት ጥናት ያመለክታል።
ኢሚግሬሽን ኤንድ ከስተመስ ኢንፎርስመንት አሊያም አይስ በመባል የሚታወቀው መሥሪያ ቤት ሕገ-ወጥ ስደተኞችን በማባረር ይታወቃል።
ከቺካጎ በተጨማሪ ኒው ዮርክ፣ ሎስ አንጀለስ፣ ዴንቨር እና ማያሚ ሕገ ወጥ ስደተኞችን የማሰስ ተግባሩ እንደሚፈፀም ዎል ስትሪት ጆርናል ስማቸውን ያልጠቀሳቸውን ምንጭ ዋቢ በማድረግ ዘግቧል።
ቺካጎ የሚገኝ በርካታ ላቲኖዎች የሚሰባሰቡበት ቤተ-እምነት ስደተኞችን በገፍ የማባረሩ ጉዳይ እንዳሳሰበው ለቢቢሲ ተናግሯል።
"እኔ በጣም ፈርቻለሁ። ወረቀት የሌላቸው ሰዎች እንዴት ሊፈሩ እንደሚችሉ አስቡት" ይላል የ21 ዓመት ሜክሲኳዊ ሕጋዊ ስደተኛ ዲ ካማቾ።
የሊንከን ዩናይትድ ሜትዲስት ቤተ-ክርስትያን አገልጋይ የሆኑት ሬቨርንድ ኤማ ሎዛኖ "አምስት ልጆች ያሏቸው ሰዎች ቢባረሩ ልጆቹን የሚንከባከበው ማነው? ቤተሰብ ሊበተን ነው ማለት ነው?" ሲሉ ይጠይቃሉ።
ምንም እንኳ የትራምፕ አስተዳደር አፈሳውን ወንጀል በፈፀሙ ስደተኞች እንደሚጀምር ቢያስታውቅም አሜሪካ ውስጥ ለበርካታ ዓመታት የኖሩ እና የሠሩ ሕገ ወጥ ስደተኞችም ታስረው ሊባረሩ እንደሚችሉ ይጠበቃል።
በርካታ ሕገ ወጥ ስደተኞች በሚሠሩባቸው የግንባታ ሥፍራዎች የሚደረገው አሰሳም እንደሚቀጥል ይጠበቃል። ይህ አሰሳ በባይደን አስተዳደር ጊዜ ተቋርጦ ነበር።












