ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ነዳጅ የጫነ ተሽከርካሪ ሆስፒታል አቅራቢያ ፈንድቶ በርካታ ሰዎች ሞቱ

ፍንዳታው

የፎቶው ባለመብት, AAA Security Group/via REUTERS

የምስሉ መግለጫ, ፍንዳታው ያስከተለው ከባድ የእሳት ቃጠሎ
ታትሟል

ከደቡብ አፍሪካዋ ጆሃንስበርግ ከተማ በስተምሥራቅ በሚገኝ አንድ ሆስፒታል አቅራቢያ አንድ ግዙፍ ነዳጅ የጫነ ተሽከርካሪ ፈንድቶ በርካታ ሰዎች ለሞት እና ለጉዳት ተዳረጉ።

ነዳጅ የጫነው ተሽከርካሪ (ቦቴ) ቅዳሜ ጠዋት ከጆሃንስበርግ ከተማ አቅራቢያ በምትገኘው ቦክስበርግ ከተማ ውስጥ ከሚገኘው የቶምቦ መታሰቢያ ሆስፒታል 100 ሜትር ርቀት ላይ ካለ መተላላፊያ ድርድይ ስር ሆኖ ነው ፍንዳታው የተከሰተው።

በፍንዳታው ቢያንስ ዘጠኝ ሰዎች ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን፣ በርካታ ቁጥር ያላቸው ደግሞ የተለያየ መጠን ያለው ጉዳት እንደደረሰባቸው የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ለሆስፒታሉ እጅግ በጣም ቅርብ በሆነ ቦታ ላይ ባጋጠመው በዚህ የነዳጅ ጫኝ ተሽከርካሪው ፍንዳታ ምክንያት፣ የሆስፒታሉ አንደኛ ክፍል ጣሪያ በመፍረሱ ህሙማን እንዲወጡ ተደርጓል።

የደቡብ አፍሪካ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት የፈነዳው ተሽከርካሪ የሲሊንደር ጋር የጫነ ነበር።

“ጋዝ የጫነው ከባድ መኪና ከመሬት በታች ባለ ትንሽዬ ድልድይ በኩል ለማለፍ ሲሞክር ተቀርቅሮ መንቀሳቀስ ባለመቻሉ በተፈጠረ ሰበቃ ምክንያት እሳት ተፈጥሮ ፍንዳታው ተከስቷል” ሲሉ የአደጋ መከላከያ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ዊሊያም ንትላዲ ተናግረዋል።

ፍንዳታውን ተከትሎ የተነሳውን የእሳት ቃጠሎ ለመቆጣጠር የእሳት አደጋ ተከላካይ ሠራተኞች ጥረት በሚያደርጉበት ጊዜ፣ ሌላ ከባድ ፍንዳታ ተከስቶ አንድ የእሳት አደጋ ማጥፊያ ተሽከርካሪን እና ሁለት መኪኖችን ሲያወድም በስፍራው በነበረ ግለሰብ የተቀረጸ ቪዲዮ አሳይቷል።

ማይክል ኩሊንጂ የተባለ የዐይን እማኝ ፍንዳታው “የቦምብ ይመስል ነበር” ሲል ከድልድዩ ስር እሳት መመልከቱን ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግሯል።

ሌላ በስፍራው የነበረች ጄን ማሪ ቦይሰን የተባለች የዐይን እማኝ ደግሞ ቅዳሜ ጠዋት አንድ ሰዓት ከመሆኑ በፊት ከባድ የእሳት ነበልባል እንደተመለከተችና ፍንዳታውም የመሬት መንቀጥቀጥ የተከሰተ እንደመሰላት ለሮይተርስ ገልጻለች።

አደጋውን ተከትሎ ወዲያውኑ የተቀረጹ የቪዲዮ ምስሎች በቃጠሎ የተጎዱ እና ግራ የተጋቡ ሰዎች ከፍንዳታው ቦታ አቅራቢያ ባለ በሚገኝ የመኖሪያ ሰፈር ውስጥ ወድቀው አሳይተዋል።