ማክሰኞ ስደተኞች ከዩኬ ወደ ሩዋንዳ የሚወሰዱበት በረራ በፍርድ ቤት ፈቃድ አገኘ

የፎቶው ባለመብት, PA Media
በመጪው ማክሰኞ ጥገኝነት ጠያቂዎችን ከዩናይትድ ኪንግደም ወደ ሩዋንዳ ለመውሰድ የሚደረገው በረራ እንዲከናወን በከፍተኛ ፍርድ ቤት ይሁኝታ ተሰጥቶታል።
የጉዞው ተቃዋሚዎች ወደ ሩዋንዳ የሚደረጉትን በረራዎች ለማስቆም ያደረጉት የመጀመሪያ ሕጋዊ ሙከራ አልተሳካላቸው። ጉዳዩን ሰኞ ወደ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት እንደሚወስዱት አረጋግጠዋል።
በተዘጋጀው ፖሊሲ መሠረት በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ዩኬ ከሚገቡት ስደተኞች መካከል የተወሰኑት የጥገኝነት ጥያቄያቸውን ከሩዋንዳ ይከታተላሉ።
ወደ 31 የሚጠጉ ሰዎች በመጀመሪያው በረራ ሊሳፈሩ እንደሚችሉ ተነግሯቸዋል።
ከፍተኛው ፍርድ ቤት ከቀጣዩ ወር መጨረሻ በፊት ፖሊሲው ላይ የቀረበውን ተቃውሞ ያዳምጣል።
ውሳኔውን የሰጡት ዳኛ ስዊፍት እንዳሉት “ለሕዝብ ጥቅም" ሲባል የአገር ውስጥ ሚንስትር ፕሪቲ ፓቴል ፖሊሲዎችን መተግበር አለባቸው።
ፓቴል ውሳኔውን በማድነቅ መንግሥት ዕቅዶቹን መተገበር ይቀጥላል ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ደግሞ ውሳኔውን “በደስታ የተቀበልኩት ዜና” ሲሉ ገልጸዋል ።
ጥያቄውን ያቀረቡት ቡድኖች “በግዳጅ ሊባረሩ” የተዘጋጁት ሰዎች ደኅንነት እንደሚያሳስባቸው አስታውቀዋል።
ታይምስ ጋዜጣ እንደዘገበው የዌልሱ ልዑል የመንግሥትን ፖሊሲ በግላቸው ሲተቹ ነበር። ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበውም አቀራረቡ "አስደንጋጭ” ነው ብለው እንደሚያስቡ አስታውቋል።
ልዑል ቻርለስ በዚህ ወር መጨረሻ በሚካሄደው የኮመንዌልዝ ስብሰባ ንሥቲቱን ወክለው በሩዋንዳ ዋና ከተማ ኪጋሊ ይገኛሉ። ጽሕፈት ቤቱ “ከፖለቲካዊ ጉዳዮች ገለልተኛ” እንደሆነ በድጋሚ ተናግሯል።
የጥገኝነት ጥያቄ ከሩዋንዳ ስለሚታይ ዕቅዱ ጥገኝነት ጠያቂዎች የዩኬ ቻናልን ለማቋረጥ ያላቸውን ተስፋ እንደሚቀንሰው መንግሥት አስቧል።
በዚህ ዓመት ብቻ ከ10,000 በላይ ሰዎች አደገኛውን የባሕር ጉዞ አድርገዋል።
ማመልከቻቸው በሩዋንዳ የሚታይ ሲሆን ስደተኞቹ መጠለያ እና ድጋፍ ይደረግላቸዋል። ከተሳካላቸውም እስከ አምስት ዓመት ድረስ የትምህርት እና የድጋፍ ዕድል እዚያው እያገኙ ሊቆዩ ይችላሉ።
በሩዋንዳ የጥገኝነት ጥያቄያቸውን ያላገኙ ሰዎች በአገር ውስጥ ለመቆየት ከፈለጉ በሌሎች የኢሚግሬሽን መንገዶች ለቪዛ እንዲያመለክቱ ዕድል ይሰጣቸዋል። ካልሆነም ሊባረሩ ይችላሉ።
ዘመቻ አድራጊዎች አውሮፕላኑ ጥገኝነት ጠያቂዎችን ይዞ እንዳይጓዝ ለመከላከል አቅደው ነበር።
ጉዳዩን ያቀረቡት የጥገኝነት ጠያቂዎቹ ጠበቆች ከኅብረተሰብ እና ንግድ አገልግሎት ማህበር (ፒሲኤስ) ጋር በመሆን ነው።
ጠበቆቻቸው በሩዋንዳ ጥገኝነት ሥርዓት ውስጥ ያሉ ጉድለቶችን እና ወደ ፍርድ ቤት ሊያመሩ ወደሚችሉባቸው አገራትም ሊላኩ ስለሚችሉበት ሁኔታ ስጋታቸውን አንስተዋል።
የአገር ውስጥ ሚንስትር ጠበቆች በበኩላቸው የሕዝብ ትቅም በመሆኑ ዕቅዱ በሕጋዊ ጉዳዮች መቆም እንደሌለበት ለፍርድ ቤቱ ነግረዋል። ዳኛው በግለሰብ ጥገኝነት ጠያቂዎች ስም እንቅፋቶቹን ውድቅ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
በችሎቱ ላይ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት (ዩኤንኤችሲአር) የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር በዕቅዱ ላይ ያለውን አቋም በተሳሳተ መንገድ አቅርቧል በሚል ራሱን ከፖሊሲው ለማራቅ ተገኝቷል።
የዩኤንኤችሲአር ጠበቆች እንዳሉት የአገር ውስጥ ሚንስትሩ ከሩዋንዳ ጋር ያደረገው ስምምነት ሕገ ወጥ ነው በማለት ሁለት ጊዜ አስጠንቅቀዋል።
"ጠንካራ አይደለም"
ዳኛ ስዊፍት በሐምሌ ወር ፖሊሲው ላይ ሙሉ ችሎት ከመሰማቱ በፊት በስደተኞች በረራዎች ላይ ጊዜያዊ እገዳ እንዲጣል መጠየቁን ውደድቅ አድርገዋል።
በዩናይትድ ኪንግደም የሰብአዊ መብት አንቀጽ ሦስት መሠረት "ድብደባ፣ በደል" ወይም መብታቸውን የሚጥስ ማንኛውም ነገር እንደሚኖር የሚያሳይ ምንም ዓይነት ማስረጃ አለ ብለው እንደማያስቡ አስታውቀዋል።
ዳኛው አክለውም የመጀመሪያውን በረራዎችን ማገድ ላይ ያተኮረው ክፍል ፓቴል “ሩዋንዳን ደኅንነትዋ እንደተጠበቀ አገር ለማድረግ ማሰባቸው ምክንያታዊ ያልሆነ ወይም በቂ ያልሆነ ጥናት ነው” በሚለው ክርክር ላይ ያተኮረ ነው ብለዋል ።
ይህ ክርክር ከሌሎች የክሱ ክፍሎች ጋር በመሆን ሐምሌ መጨረሻ በሚቀርበው ችሎት ላይ እንደሚታይ ተናግረዋል።
አመልካቾች ለግምገማ በቂ ማስረጃ ቢኖራቸውም ጥያቄያቸው “በጉልህ ጠንካራ አይደለም” ብለዋል።
በተጨማሪም ማክሰኞ ወደ ሩዋንዳ በሚደረገው በረራ ላይ እንደሚሳፈሩ የተነገራቸው አንድ የሶሪያ እና አንድ የኢራቅ ዜጋ የእፎይታ ጊዜ ይሰጣቸው የሚለውንም ውድቅ አድርገውታል።
አክለውም "ወደ ሩዋንዳ የመወሰዱ እውነታ ከባድ እንደሚሆን እቀበላለሁ" ብለዋል።
ዳኛው ለዘመቻው አራማጆች እና ለስደተኞቹ በሰጡት ውሳኔ ላይ ይግባኝ የመጠየቅ መብት ሰጥተዋል። ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ሰኞ ጉዳያቸውን ማየት ይችላልም ብለዋል።












