የቼልሲው አለቃ ግራሃም ፖተር በቅጡ ሰባት ወር ሳይሞላቸው ተሰናበቱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቅዳሜ ቼልሲ በአስቶን ቪላ 2 ለ 0 መሸነፉን ተከትሎ አሰልጣኝ ግርሃም ፖተር ሰባት ወራት በቅጡ ያልያዙትን መንበር እንዲለቁ ተደርጓል።
ቶማስ ቱሄልን ተክተው ስታምፎርድ ብሪጅ የደረሱት እንግሊዛዊው ከ31 ጨዋታዎች በ11ዱ ተሸንፈዋል።
ለተጫዋቾች ዝውውር ከ550 ሚሊዮን ፓውንድ በላይ ያወጣው ቼልሲ 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። በቀጣዩ ዓመት በሻምፒዮንስ ሊግ የመሳተፉ ዕድልም ተመናምኗል።
የክለቡ ባለቤቶች ፖተር በመሰናበታቸው “አዝነናል” ብለዋል።
ፖተር “ከክለቡ ጋር በመተባበር ሽግግሩን ለማሳለጥ ተስማምተዋል” ሲል ክለቡ ገልጿል።
ከፖተር ጋር በአሰልጣኝነት በብራይተን የሠሩት ብሩኖ ሳለተር ተጠባባቂ አሰልጣኝ ሆነው ተሹመዋል።
የክለቡ ባለሃብቶች ከሆኑት መካከል ቶድ ቦሄይል እና ቤህዳድ ኤግባሊ “እንደ አሰልጣኝም ሆነ እንደ ግለሰብ ለግርሃም ትልቅ ክብር አለን” ብለዋል።
ቼልሲ ነገ ማክሰኞ ሊቨርፑልን በሜዳው ያስተናግዳል። ከዘጠኝ ቀን በኋላ በሻምፒዮንስ ሊግ ሩብ ፍጻሜ የመጀመሪያ ጨዋታ ከማድሪድ ጋር ያደርጋል።
በዘንድሮው የውድድር ዓመት በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 13 አሰልጣኞች ተሰናብተዋል። ይህም ከየትኛውም የሊጉ የውድድር ዓመት በሦስት ይበልጣል። ሌስተር እሑድ ዕለት በተመሳሳይ አሰልጣኝ ብሬንዳን ሮጀርስን ማሰናበቱ ይታወሳል።
“ከአስገራሚዎቹ ደጋፊዎቻችን ጋር ለብሩኖ ድጋፍ በመስጠት እስክ ውድድር ዓመቱ ፍጻሜ እንጓዛለን” ሲሉ የክለቡ ባለቤቶች አክለዋል።
“10 የሊግ ጨዋታዎች ይቀሩናል። በሻምፒዮስ ሊግም እንሳተፋለን። በመተባበር ከእያንዳንዱ ጨዋታ ጥሩ ውጤት በማስመዝገብ ዓመቱን በከፍተኛ ደረጃ ለማጠነማቀቅ እንጥራለን።“
ፖተር ከ31 ጨዋታዎች 12 ብቻ አሸንፈዋል።
ፖተር በብራይተን ከነበራቸው ሦስት ስኬታማ ዓመታት በኋላ ነው በአዲሱ የቼልሲ ባለቤት አማካይነት ወደ ምዕራብ ለንደኑ ክለብ ያቀኑት።
ፖተር በ20 ወራት የብሪጅ ቆይታቸው ሦስት ዋንጫ ለመሳም የበቁትን ቶማስ ቱህልን ተክተውነው ቼልሲ የደረሱት።
ክለቡ በጥር የዝውውር መስኮት 288 ፓውንድ ለተጫዋቾች ግዢ አውጥቷል።
ኤንዞ ፈርናንዴዝ እና ማይክይሎ ሙድርኪ ከስምንቱ የጥር ፈራሚዎች መካከል ናቸው።
ቼልሲ ቤት ነገሮች በፍጥነት ተቀያይረዋል። ከሊቨርፑል ጨዋታ በፊት ዛሬ ፖተር ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጡ እሑድ ጠዋት መልዕክት ለጋዜጠኞች ተልኮ ነበር። እሑድ ምሽት ፖተር ተሰናበቱ።
የስንብቱ ውሳኔ ከደካማ ውጤት ጋር ብቻ የተያያዘ ሳይሆን ቡድኑ ለውጥ አለማሳየቱም ጭምር መሆኑ ተነግሯል።
በስንብቱ ምክንያት ፖተር ለአምስት ዓመት የፈረሙትን ሙሉ ክፍያ እንደማያገኙ ተነግሯል።
አዲስ አሰልጣኝ የመፈለግ ሥራው የተጀመረ ሲሆን በቀናት ውስጥ ይፋ እደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።












