ኢራን በፕሬዝዳንቷ ሞት ምክንያት ለአምስት ቀናት የሚቆይ ብሔራዊ ሃዘን አወጀች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የኢራኑ ሃይማኖታዊ መሪ አያቶላ አሊ ካሜኒ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲን ህልፈት ተከትሎ አምስት ብሔራዊ የሃዘን ቀናትን አውጀዋል።
ራይሲ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆሴን አሚር አብደላሂ ጋር በሰሜን ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍል ሄሊኮፕተር ተከስክሶ ህይወታቸው አልፏል።
እሑድ ዕለት ይጓዙበት የነበረው ሄሊኮፕተር መከስከሱን ተከትሎ ህይወታቸው ማለፉን የአገሪቱ መንግስት መገናኛ ብዙሃን አረጋግጠዋል።
አያቶላህ ካሜኒ “ለተወዳጁ የኢራን ህዝብ” ሃዘናቸውን ገልፀዋል።
የ63 ዓመቱ ራይሲ ሃይማኖታዊ መሪውን ሊተኩ ይችላሉ የሚል ግምት ነበር።
አዲስ ፕሬዝዳንት ለመምረጥ ሰኔ 28 ምርጫ እንደሚካሄድ የአገሪቱ መንግስት መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።
ይህ በእንዲህ እያለ ምክትል ፕሬዝዳንት መሐመድ ሞክበር በጊዜያዊነት ፕሬዝዳንት ሆነው እንዲሠሩ ተሹመዋል።
የኢራን ካቢኔ በበኩሉ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሊ ባገሪ ካኒንን ጊዘያዊ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አድርጎ ሾሟል።
መጀመሪያ ላይ መሪዎቹን እና አጃቢዎቻቸውን የጫነችው ሄሊኮፕተር ጭጋጋማ በሆነ አካባቢ አደጋ እንደደረሰባት ተዘገበ።
አደጋው ያጋጠመበት አካባቢ ለአዘርባጃን ድንበር ቅርበት ያለው ነው። ራይሲም ከአገሪቱ ፕሬዝዳንት ኢልሃም አሊዬቭ ጋር ተገናኝተው እየተመለሱ ነበር።
እንደ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘገባ ከሆነ ራይሲ ወደ ስፍራው ያቀኑት የኪዝ ቃላሲ እና ኮዳፋሪን ግድቦችን ለመመረቅ ነበር።
የኢራን ቀይ ጨረቃ ሰኞ ዕለት እንዳስታወቀው የፕሬዚዳንቱን እና በአደጋው የሞቱት ሰዎች አስከሬን መገኘቱን እና የፍለጋ ሥራው መጠናቀቁን አረጋግጧል።
የድርጅቱ ዋና ኃላፊ በመንግስት ቴሌቪዥን ላይ ቀርበው "የሰማዕታቱን አስከሬን ወደ ታብሪዝ (የኢራን ሰሜናዊ ምዕራብ ከተማ) ለማዛወር በሂደት ላይ ነን" ብለዋል።
የኢራኑ የዜና አውታር ታስኒም በበኩሉ የፕሬዚዳንት ኢብራሂም ራይሲ የቀብር ስነ ስርዓት ማክሰኞ በታብሪዝ እንደሚፈጸም ዘግቧል።
የራይሲን መሞት ተከትሎ የኢራን መንግስት በሰጠው መግለጫ “ያለምንም መስተጓጎል” የአገሪቱ መንግስት ሥራ እንደሚቀጥል አስታውቋል።
የፕሬዚዳንት ራይሲን ሞት ተከትሎ በርካታ አገራት ሃዘናቸውን ገልጸዋል።
የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሼህባዝ ሻሪፍ ብሔራዊ የሃዘን ቀን ያወጁ ሲሆን ራይሲን እና አሚር አብዶላህያንን "የኢራን ጥሩ ወዳጆችች" ሲሉ ገልፀዋቸዋል።
የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በበኩላቸው “በጣም ማዘናቸውን እና መደናገጣቸውን” በማህበራዊ ሚዲያ ገልጸዋል።
የቱርክ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን ደግሞ መንግስታቸው "ከኢራን ባለስልጣናት ጋር ሙሉ ግንኙነት እና ቅንጅት እያደረገ" እና "አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ" ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ቱርክም ብሔራዊ የሃዘን ቀን ታውጃለች ብለዋል።
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ሃዘናቸውን ገልጸው፤ ፕሬዚዳንቱ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እውነተኛ እና ታማኝ የአገራችን ወዳጆች ናቸው ብለዋል። የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ በበኩላቸው ራይሲ ለኢራን ደህንነት እና መረጋጋት አስተዋጽኦ አድርገዋል ብለዋል።
የአውሮፓ ህብረት ሰኞ ዕለት ባወጣው መግለጫ "ልባዊ ሃዘኑን" የገለጸ ሲሆን የአውሮፓ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ቻርልስ ሚሼል በበኩላቸው "ቤተሰቦቻቸው መጽናናትን ተመኝተዋል።"
ሐማስ ራይሲ ለፍልስጤሙ ቡድን ያደረጉትን ድጋፍ አድንቋል። በሊባኖስ የሚገኘው እና በቴህራን የሚደገፈው የሄዝቦላህ በበኩሉ በጠባቂው ሞት ማዘኑን ገልጿል።
ዋይት ሃውስ ደግሞ ሟቹ ኢራን "ለአካባቢው የሽብር ቡድኖች” በምታደርገው ድጋፍ ፕሬዝዳንቱ ተጠያቂ እንደነበሩ እና "ብዙ ደም በእጃቸው ላይ እንዳለ" አስታውቋል።
የዋይት ሃውስ የብሔራዊ ደህንነት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ እንደተናገሩት የኢራኑ መሪ "በገዛ አገራቸው ለደረሰው አሰቃቂ የሰብአዊ መብት ጥሰት" ተጠያቂ ናቸው።
"በመቶዎች በሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች ላይ የተፈጸመው እስር እና አካላዊ ጥቃት" እንደምሳሌ አንስተዋል።
"በእርግጥ ኢራን በአካባቢው ለሚገኙ የአሸባሪ ቡድኖች ለሰጠችው ድጋፍ ተጠያቂው እሱ ነው" ብለዋል።












