ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትራምፕ የጆ ባይደንን የደኅንነት መረጃዎችን የማግኘት እና ሌሎች መብቶችን እንደሚያግዱ አሳወቁ
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንን ከደኅንነት ጋር የተያዙ መብቶች እና በየዕለቱ ይደርሷቸው የነበሩትን የደኅንነት መረጃዎችን እንዳያገኙ እንደሚከለክሉ አስታወቁ።
ጆ ባይደን በሥልጣን ላይ በነበሩበት ጊዜ ከአራት ዓመት በፊት የአሁኑ ፕሬዝዳንት ላይ ተመሳሳይ እርምጃ ወስደው ነበር።
"ጆ ባይደን ምሥጢራዊ መረጃዎችን ማግኘት እንዲቀጥል አያስፈልግም" ሲሉ ትራምፕ ትሩዝ በተሰኘው ማኅበራዊ ሚድያ ገጻቸው ላይ ባጋሩት ጽሑፍ ላይ አስታውቀዋል።
የሪፐብሊካን አባላት በበኩላቸው ይህንን መረጃ ተከትለው ከዚህ ቀደም ፕሬዝዳንት ትራምፕ ይሳተፉበት በነበረው 'The Apprentice' የቴሌቪዥን ሾው ላይ ይጠቀሙበት የነበረውን ሐረግ በመዋስ "ጆ፣ ተባርረሃል" ሲል ተሳልቀዋል።
ትራምፕ በአውሮፓውያኑ 2020 በተደረገው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ለጆ ባይደን በመወገን ጣልቃ ገብተዋል ያሏቸውን በርካታ የቀድሞ የደኅንነት መሥሪያ ቤቱ አባላት ወቅታዊ የደኅንነት መረጃዎች እንዳይደርሷቸው አግደዋል።
ትራምፕ አርብ ማምሻውን በማኅበራዊ ድረ ገጻቸው ባጋሩት መረጃ ባይደን "በ2021 ለደኅንነት ማኅበረሰቡ 45ኛው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት (እኔ) ለቀድሞ ፕሬዝዳንቶች የተፈቀደውን በብሔራዊ ደኅንነት ላይ ዝርዝር መረጃዎችን እንዳያገኝ ሲያስቆም ይህንን አሠራር ተግባራዊ ማድረግ ጀምሯል" ብለዋል።
በዲሞክራቶች የተከማቹ እና የፍትህ ሚኒስቴር ምርመራ የጀመረባቸውን ምስጢራዊ ሰነዶችን በመጥቀስ ባይደን "ምስጢራዊ በሆኑ መረጃዎች ሊታመን አይችልም" ካሉ በኋላ ክስ ላለመመሥረት መወሰኑን ገልጸው፤ "ባይደን የማስታወስ ችግር አለበት" ብለዋል። ባይደን በወቅቱ ይህንን ውንጀላ አልተቀበሉትም ነበር።
ባለፈው ወር ሥልጣናቸውን ያስረከቡት ጆ ባይደን በጉዳዩ ላይ ምላሽ አልሰጡም።
ቢቢሲ በጉዳዩ ላይ ምላሽ ለማግኘት አብሯቸው የሚሠራውን ኤጀንሲ ለማነጋገር ያደረገው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።
በ2021 ባይደን ትራምፕ ምሥጢራዊ የደኅንነት መረጃዎችን እንዳያገኙ አግደው ነበር።
የትራምፕ ደጋፊዎች በአሜሪካ ምክር ቤት ላይ ወረራ ከመፈጸማቸው በፊት ዴሞክራቶች ትራምፕን በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው የመጨረሻ ቀናት ውስጥ ያሳይዋቸውን ባህሪያት በመጥቀስ በደኅንነት መረጃዎች ላይ ሊታመኑ እንደማይችሉ በመግለጽ ለውሳኔው ድጋፋቸውን ሰጥተዋል።
"የደኅንነት መረጃዎችን መስጠት ምን ዋጋ አለው?" ሲሉ ነበር በወቅቱ ባይደን የተናገሩት። "እሱ አምልጦት አንድ ነገር ሊናገር ከመቻል ውጪ ምን ተጽእኖ ይኖረዋል?"
ትራምፕ የፕሬዝዳንትነት ሥልጣናቸውን ከተረከቡ በኋላ ከባይደን አስተዳደር ጋር የተገናኙ ሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናትን የደኅንነት መረጃዎች እና ከለላዎችን እንዳያገኙ አድርገዋል።
ከእነዚህም መካከል የትራምፕ ቀንደኛ ተቺ የሆኑት የቀድሞው የአሜሪካ ከፍተኛ ጦር አዛዥ ማርክ ሚሌይ ይገኙበታል።
አዲሱ የመከላከያ ሚኒስትር ፔት ሄግሰትም የሚሊ "ምግባር" እንዲመረመር እና የውትድርና ማዕረጋቸውም ዳግመኛ እንዲታይ አዝዘዋል።
ትራምፕ የቀድሞ የፕሬዚዳንቱ ዋና የጤና ጉዳዮች አማካሪ የነበሩትን እና የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምላሽን በግንባር ቀደምትነት የመሩትን ዶክተር አንቶኒ ፋውቺን የተመደበላቸውን ጥበቃ አንስተዋል።
ትራምፕ በወቅቱ ውሳኔው "ተገቢ እና የተለመደ" ነበር ያሉ ሲሆን፣ ሁሉም ሰው ለመንግሥት ስለሠራ ብቻ በቀሪ የሕይወት ዘመኑ የደኅንነት ጥበቃ እና ከለላ ማግኘት አይችልም ሲሉ ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንቱ በተጨማሪም ሁለት የቀድሞ የሲአይኤ ዳይሬክተሮችን ጨምሮ በርካታ የቀድሞ የስለላ መሥሪያ ቤቱ ባለሥልጣናት የነበራቸው ጥበቃ እንዲነሳ ትዕዛዝ ሰጥተዋል።