ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአርሰናል እና በሲቲ ጨዋታ ሰበብ በግድያ የተጠረጠሩ ሁለት ኡጋንዳውያን ተያዙ
በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ የአርሰናል እና ማንችስተር ሲቲ ጨዋታን ተከትሎ በተከሰተ ጸብ ካምፓላ ውስጥ በአንድ ወጣት ሞት ሁለት የሲቲ ደጋፊዎች በግድያ ወንጀል ተይዘው ሊከሰሱ ነው።
በጨዋታው አርሰናል አንድ ለዜሮ በማንችስተር ሲቲ ከተሸነፈ በኋላ በተፈጠረው ጸብ ውስጥ ጣልቃ የገባ ወጣት አርብ ዕለት በስለት ተወግቶ ሕይወቱ አልፏል።
የኡጋንዳው ዴይሊ ሞኒተር ጋዜጣ እንደዘገበው አለን ካኩምባ የተባለው ወጣት ጉዳቱ ደርሶበት ሆስፒታል ከገባ ከአንድ ቀን በኋላ ነው ሕይወቱ ያለፈው።
ፖሊስ ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው ከግድያው ጋር በተያያዘ ሁለት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።
የዋና ከተማዋ ካምፓላ ፖሊስ ቃል አቀባይ ተጠርጣሪዎቹ በቅርቡ ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በ25 ዓመቱ ወጣት ካኩምባ የተገደለው የአርሰናል ደጋፊ የሆነው ወንዱሙ ከማንችስተር ሲቲ ደጋፊዎች ጋር በተጋጨበት ጊዜ ጣልቃ ገብቶ በነበረበት ጊዜ በስለት ተወግቶ ነው።
ይህ ሁኔታ የተከሰተው በኡጋንዳ ዌስት ናይል ወረዳ ውስጥ አንድ የአርሰናል ደጋፊ በአሰቃቂ ሁኔታ ጥቃት ተፈጽሞበት ከተገደለ ከቀናት በኋላ ነው።
ግድያው ከሳምንት በፊት አርሰናል ከማንችስተር ዩናይትድ ጋር ባደረገው ግጥሚያ በዩናይትድ ሽንፈት የተበሳጨ አንድ ደጋፊ የአርሰናሉን ደጋፊ ከኋላው ጭንቅላቱን መትቶት የተፈጸመ ነው ተብሏል።
ፖሊስ እንዳለው ሟቹ በአካባቢው የሚታወቅ የአርሰናል ደጋፊ ነበረ ሲሆን፣ በጨዋታው ወቅት አርሰናል ባስቆጠራት የመጨረሻ ደቂቃ ግብ ምክንያት ውዝግብ ውስጥ ገብቶ እንደነበር ተዘግቧል።
ሟች ጥቃቱ ከተፈጸመበት በኋላ ወደ አካባቢው ጤና ጣቢያ ቢወሰድም ሕይወቱ ሳይተርፍ ቀርቷል።
በበርካታ የአፍሪካ አገራት ውስጥ እንደሚታየው የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ እግር ኳስ ውድድር በኡጋንዳ ውስጥም በጣም ተወዳጅ ነው።
የእግር ኳስ ጨዋታው ተወዳጅነትን በአፍሪካ ውስጥ የበለጠ እንዲጨምር ያደረገው እየተስፋፋ ያለው የውርርድ ቁማር መሆኑን የቀድሞው የኡጋንዳ የስፖርት ጋዜጠኞች ማኅበር ኃላፊ ጆሴፍ ካቡሌታ ተናግሯል።
በዚህም ምክንያት የእግር ኳሱ አፍቃሪዎች ገንዘባቸውን በውርርድ ስለሚያሲዙ የጨዋታዎችን ውጤቶች በቀላሉ አይመለከቷቸውም። ይህ ደግሞ ስሜታዊ እንዲሆኑ ስለሚያደርጋቸው ወደ ጸብ እና ወንጀል እንደሚያመራ ጆሴፍ ለቢቢሲ ተናግሯል።
በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ የበላይነትን የያዘው አርሰናል ከጥቂት ሳምንታት በፊት ማንችስተር ሲቲን 3 ለ 2 ባሸነፈበት ጊዜ፣ በምሥራቃዊ ኡጋንዳ ጂንጃ ከተማ ውስጥ ደስታቸውን አደባባይ ለመግለጽ የወጡ ስምንት የአርሰናል ደጋፊዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ነበር።
እነዚህ የአርሰናል ደጋፊዎች በጉዳናዎች ላይ በመዘዋወር የዩናይትድን ደጋፊዎች ለማብሸቅ ፈልገው ነበር፤ ነገር ግን ፖሊስ ድርጊታቸው ፈቃድ ያላገኘ ነው በማለቱ ለአንድ ቀን አስሮ ለቋቸዋል።