ተጠርጣሪ ሲደበደብ የሚያሳይ ቪድዮ ከወጣ በኋላ 3 ፖሊሶች ታገዱ

ፖሊሶች ተጠርጣሪውን ሲደበድቡ

የፎቶው ባለመብት, TIKTOK

ታትሟል

አንድ ተጠርጣሪ መሬት ላይ ተዘርሮ በተደጋጋሚ ሲደበደብ የሚያሳይ ቪድዮ መውጣቱን ተከትሎ ሦስት የአርካንሳስ ፖሊሶች ከሥራ ታገዱ።

ከፖሊሶቹ አንዱ ተጠርጣሪውን በተደጋጋሚ ጭንቅላቱን በቡጢ ሲደበድበውና ከአስፋልት ጠርዝ ጋርም ጭንቅላቱን ሲያጋጨው ቪድዮው ያሳያል።

ሌላው ፖሊስ የግለሰቡን ጀርባ በጉልበቱ ሲመታ ይታያል።

ሁለቱም ፖሊሶች የደንብ ልብስ ያደረጉ ናቸው።

ሁለቱ ፖሊሶች ግለሰቡን ሲደበድቡ ሦስተኛው ፖሊስ ግለሰቡን መሬት ላይ ተጭኖ ይዞት ይታያል።

ግለሰቡ በፖሊሶቹ ሲደበደብ ፊቱን ሸፍኖ ራሱን ለመከላከል ሲሞክር ይታያል። ሰውነቱን ጠቅልሎ ራሱን ከድብደባው ለመከላከልም ይሞክራል።

ቪድዮውን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ያዩት ሲሆን፣ ከፍተኛ ቁጣም አስነስቷል።

ከሁለት ዓመት በፊት በፖሊስ የተገደለው ጆርጅ ፍሎይድ ጉዳይም ዳግመኛ እንዲነሳ አድርጓል።

ፍሎይድ በገደሉን ተከትሎ በአሜሪካና በሌሎችም አገራት ከፍተኛ ተቃውሞ መነሳቱ አይዘነጋም።

ቪድዮው ላይ ፊቷ የማይታይ ሴት “አትደብድቡት፣ መድኃኒቱን ይፈልጋል” ስትል ይሰማል።

አንደኛው ፖሊስ ሴቲቷ ወደ መኪናዋ እንድትገባ ሲናግር፣ ሌላው ፖሊስ ሲሳድብ ይሰማል።

ቪድዮውን የለጠፈችው ግለሰብ ድርጊቱ በሜልበሪ ሲፈጸም እህቷ እንዳየች ገልጻለች።

ፖሊስ እንዳለው ራንዳል ዎርስተር የተባለው ግለሰብ በቁጥጥር ሥር የዋለ ሲሆን፣ 27 ዓመቱ ነው።

አንድ ሱቅ ውስጥ አስፈራርቷል በሚል ተጠርጥሮ ነው የታሰረው።

ፖሊሶች ግለሰቡን ለመያዝ በሄዱበት አንዱን ፖሊስ መሬት ላይ እንደገፈተረውና ከኋላው ጭንቅላቱን እንደመታው ተገልጿል።

በቁጥጥር ሥር የዋለውም ከዚህ በኋላ እንደሆነ ፖሊስ ገልጿል።

ፖሊስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ተጠርጣሪው ወደ ሆስፒታል የተወሰደ ሲሆን፤ በማስፈራራት፣ በቁጥጥር ሥር ሊውል ሲል በመታገልና አካላዊ ጥቃት በመሰንዘር እንደሚከሰስ ተገልጿል።

የክራውፎርድ ግዛት የፖሊስ ኃላፊ ጂሚ ዳማንቴ እንዳሉት ሁለት የአካባቢው ምክትል ፖሊሶች እንዲሁም አንድ ሌላ ፖሊስ ከሥራ ታግደው ክስተቱ ላይ ምርመራ ይካሄዳል።

“ሁሉም ሠራተኞቼ ለድርጊታቸው ኃላፊነት እንዲወስዱ አደርጋለሁ። ተገቢውን እርምጃም እወስዳለሁ” ብለዋል።

የሜልበሪ ፖሊስ ኃላፊ ሻኖን ግሪጎሩ በበኩላቸው “የሜልበሪ ግዛት ለምርመራው ከፍተኛ ቦታ ይሰጣል” ብለዋል።