አርሰናል፣ ሊቨርፑል እና ዩናይትድ ወደ ድል ይመሰሉ ይሆን. . . የሳምንቱ የፕሪሚየር ሊግ ግምቶች

ታትሟል

ባለፈው የካቲት ሊድስ ወደ ሊቨርፑል አቅንቶ ነበር።

6 ለ 0 ተሸነፈ። ከቀናት በኋላ ደግሞ አሰልጣኝ ማርሴሎ ቤልሳን አሰናበተ።

በዚህ ሳምንትም ታሪክ ራሱን ይደግም ይሆን?

የቢቢሲው እግር ኳስ ተንታኝ ክሪስ ሱቶን  “ጄሴ ማርሽ አደጋ ውስጥ ነው። የሊድስ ደጋፊዎች የቤልሳን ስም ሲጠሩ መስማት ለማርሽ የሚጠቅመው ነገር የለም” ይላል።

“ዘንድሮ ሊድስ በአንዳንድ ጨዋታዎች ማግኘት የሚገባውን ነጥብ አላገኘም። ሌላ ጊዜ ደግሞ አቋሙ ወርዷል። አስልጣኙን የጎዳው ሌላው ነገር ከአንዳንድ ሸንፈቶች በኋላ ጥሩ ሳይሆኑም መልካም ጎኖችን አይቻለሁ ማለታቸው ነው” ሲል ያክላል።

ለመሆኑ 13ኛው ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚር ሊግ ጨዋታዎች በምን መልኩ ይጠናቀቃሉ? ሱቶን ግምቶቹን አስቀምጧል።

ቅዳሜ

ሌስተር ከ ማንቸስተር ሲቲ

ኤርሊንግ ሃላንድ መጫወቱ እርግጥ አለመሆኑ ይህንን ግምት ከባድ ያድርገዋል። ሲቲ ካለአጥቂው በተለየ መንገድ መንቀሳቀስ አለበት።

ሌስተር በሳምንቱ አጋማሽ ካለመጫወቱም በላይ ተከላካይ ክፍሉን ጨምሮ ጀምስ ማዲሰን እና ሃርቪ ባርነስ ድንቅ አቋም ላይ ይገኛሉ።

ይህም ቢሆን ግን ሲቲ የበላይነቱን የሚይዝበት ስብስብ አለው።

ግምት፡ 1 – 3

ብርንማውዝ ከ ቶተንሃም

ከቶተንሃም ምን መጠበቅ እንዳለብኝ ማወቅ ስለሚያስቸግር ይህንንም ጨዋታ ለመገመት ከባድ ያደርገዋል።

በሳምንቱ አጋማስ ከስፖርቲንግ ሊዝበን ጋር አቻ ተለያይቷል። ለዚህ ጨዋታ ደካማውን መጀመሪያ አጋማሽ ወይስ ለማሸነፍ ከጫፍ ደርሶ የነበረው የሁለተኛው አጋማሽ አጨዋወት ይታያል የሚለው አይታወቅም።

አሰልጣኝ አንቶኒዮ ኮንቴ ቡድናቸው መድከሙን መናገራቸው ጥሩ መልዕክት አያስተላልፍም።

በርንማውዞች በዌስትሃም በተሸነፉበት ጨዋታ ቫር ከጎናቸው የቆመ አይመስልም። ከተከታታይ ሽንፈት በኋላ አንድ ነገር ማግኘት ቢጠበቅባቸውም ከሽንፈት አያመልጡም።

ግምት፡ 0 – 1

ብሬንትፎርድ ከ ዎልቭስ

ሁለቱም ቡድኖች ባለፈው ሳምንት ቢሸነፉም ብሬንትፎርድ የሚያንሰራራ ይመስለኛል።

በሜዳቸው ጥሩ የሆኑት ብሬንትፎርዶች ውጤጥ እንደሚያገኙ እገምታለሁ።

የዎልቭስ ጊዜያዊ አሰልጣኝ የሆኑት ስቲቭ ዴቪስ እስከ ፈረንጆቹ አዲስ ዓመት በሥራቸው የሚቆዩ መሆናቸው ቢረጋገጥም አሁንም ስጋት ቡድኑ ላይ እንዳንዣበበ ነው።

ጥሩ ጥሩ ተጫዋቾችን ቢይዙም በሌስተር ከደረሰባቸው ሽንፈት በኋላ ምን ያጋጥማቸው ይሆን የሚል ስጋት ፈጥሯል።

ግምት፡ 2 – 1

ብራይተን ከ ቼልሲ

አሰልጣኝ ሮቤርቶ ደ ዜርቢ የመጀመሪያ ድላቸውን ከብራይተን ጋር ለማስመዝገብ እየጠበቁ ነው።

ለዚህ ደግሞ የቀድሞውን አሰልጣኝ ግራህም ፖተርን በሜዳቸው ያስተናግዳሉ።

ፖተርም ያለፉትን ዘጠኝ ጨዋታዎች ባይሸነፉም ይህ ጨዋታ ቀላል አይሆንላቸውም።

ብዙ ቡድኖች በሲቲ ሲሸነፉ የሚወሰድባቸውን ዓይነት የበላይነት ብራይተኖች ላይ አላሳዩም።

ግምት፡ 1 – 1

ክሪስታል ፓላስ ከ ሳውዝ ሃምፕተን

ሳውዝሃምፕተኖች ባለፈው ሳምንት ከአርሰናል ጋር በነበራቸው ጨዋታ በሁለተኛው አጋማሽ ጥሩ ነበሩ። መድፈኞቹ በመጀመሪያው አጋማሽ ጨዋታውን ማጠናቀቅ ነበረባቸው።

ይህ ግን የቡድን አቋም ነው። 90 ደቂቃ ወጥ አቋም አያሳዩም።

ክሪስታል ፓላሶች ባለፈው ሳምንት በኤቨርተን ቢበለጡም በሜዳቸው ጠንክረው እንደሚመለሱ እገምታለሁ።

ዊልፍሬድ ዛሃ ባለፈው ዓመት ሳውዝሃምፕተን ላይ በሜዳውም ሆነ ከሜዳው ውጭ ጎሎችን አስቆጥሯል። በዚህ ጨዋታውም  ልዩነት ሊፈጥር እንደሚችል ምልክት ሊሆን ይችላል።

ግምት፡ 2 – 1

ኒውካስል ከ አስቶን ቪላ

አስቶን ቪላ ኡናይ ኤምሬን አስለጣኙ አድርጎ ሾሟል። ቡድኑ ግን በተጠባባቂ አለስጣኝ አሮን ዳንክስ ባለፈው ሳምንት ብሬንትፎርድን 4 ለ 0 አሸንፏል።

ይህ ለቪላ ትልቅ ድል ነው።

ኒውካስል በአሰልጣኝ ኤዲ ሆዊ ስር እያሳየ ያለው ለውጥ አስደምሞኛል።

ዕድለ ቢስ ባይሆኑ ከዚህም የተሻለ ነጥብ መሰብሰብ ይችሉ ነበር።

ግምት፡ 2 – 0

ፉልሃም ከ ኤቨርተን

ኤቨርተኖች በአሰልጣኝ ፍራንክ ላምፓርድ ስር ጥሩ መንቀሳቀስ ጀምረዋል።

ዘንድሮ በተደጋጋሚ ይሸነፋሉ ብልም ፉልሃሞችም ጥሩ አቋም ላይ ይገኛሉ።

የማርኮ ሲልቫ ቡድን በሜዳውም ሆነ ከሜዳው ውጭ ጥሩ ቡድን ነው።

ሁለቱም ቡድኖች ሊያሸንፉ ይችላሉ ማለት ቢቻልም እኔ አቻ ብዬ እገምታለሁ።

ግምት፡ 1 – 1

ሊቨርፑል ከ ሊድስ

የሊድስ መጥፎ ውጤት በጄሴ ማርስ ላይ ብቻ የሚሳበብ አይመስለኝም። ከዚህ ጨዋታ ግን ጥሩ ነገር ይጠብቃሉ።

ዘንድሮ ሊቨርፑል አለ ሲባል የሌለ ቡድን መሆኑን በተደጋጋሚ አሳይቷል።

በቻምፒዮንስ ሊግ ከአያክስ ጋር ድንቅ ምሽት ያሳለፉ ሲሆን ይህም ጨዋታ በሜዳቸው መሆኑ ያግዛቸዋል።  

ይህን ጨዋታ ሊቨርፑል በቀላሉ ያሸንፋል የሚል ግምት አለኝ።

ግምት፡ 6 – 1

እሑድ

አርሰናል ከ ኖቲንግሃም ፎረስት

ይህ ጨዋታ በሊጉ መሪ እና በግርጌ በሚገኙ ክለቦች መካከል የሚከናወን ነው።

አርሰናል በሳውዝሃምፕተኑ ጨዋታ ሁለተኛ አጋማሽ የደከመ ይመስላል። በዚያ ላይ ሐሙስ ዕለት ከፒኤስቪ ጋር ተጫውቷል። ይህም ቢሆን ጨዋታውን ያሸንፋል።

ፎረስቶች ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች በመከላከል ረገድ የተሻሉ በመሆናቸው ጎል አላስተናገዱም።

ይሁን እንጂ ጨዋታው በመድፈኞቹ ሜዳ የሚካሄድ ስለሆነ መድፈኞቹ ያሸንፋሉ ብዬ እገምታለሁ። ቀጣይ ጨዋታዎች ግን ቡድኑን ዕጣ ፈንታ ይወስናሉ።

ግምት፡ 2 – 0

ማንቸስተር ዩናይትድ ከ ዌስት ሃም

የራፋኤል ቫራን መጎዳት እና ጂያንሊካ ስካማካ አቋም ስጋት ቢፈጥርም ማንቸስተር ዩናይትድ ጨዋታውን የሚያሸንፍ ይመስለኛል።

ዌስትሃም ጠንካራ የመከላከል አቋም ላይ ቢገኝም ማንቸስተርን የማጥቃት እንቅስቃሴ የሚቋቋም አይመስልም።

የዩናይትዱ አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግ መሻሻሎችን ቢያስመዘግቡ የሮናልዶ ጉዳይ ትኩረት እየሳበ ነው።

ሮናልዶም በኦልድትራፎርድ ያለውን ስም እያጠለሸ ይመስላል።

ግምት፡ 2 – 1