ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሩሲያ ባለፉት ሁለት ቀናት ብቻ በርካታ ድሮኖችን ማሰማራቷን ዩክሬን ገለጸች
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ሩስያ በሁለት ቀናት ውስጥ ብቻ ወደ 30 የሚጠጉ የድሮን ጥቃቶችን መፈጸሟን ተናገሩ።
በአጠቃላይ እስካሁን ድረስ ሩሲያ 4500 የሚሳዬል ጥቃቶችን እና 8000 የአየር ዘመቻዎችን ማድረጓን ተናግረዋል።
ዘለንስኪ የተመታች የኢራን ስርሪት የሆነች ድሮን ጎን ቆመው በሰጡት መግለጫ ላይ ''ክንፋቸውን እንመታቸዋል'' ሲሉ የሩሲያን የአየር ጥቃት አቅም ለማዳከም ዝተዋል።
የምዕራቡ አገር መሪዎች ኢራን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ድሮን ለሩሲያ እያቀረበች ነው ቢሉም ሞስኮ እና ቴህራን ግን ይህንን ያስተባብላሉ።
የአሜሪካው የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን የሩሲያን የድሮን ጥቃት ''አሰቃቂ'' ሲሉ ጠርተውታል።
ብሊንከን የሩሲያ የጦር አዛዦችን በድሮን ጥቃቶች ሲቪሎችን በመግደል እና ሲቪል ሰዎች የሚጠቀሙባቸውን እንደ ኤሌክትሪክ፣ ውሃ እንዲሁም የቤተ ማሞቂያ መሠረት ልማት በማውደም ከሰዋቸዋል። ይህንን ያሉት በካናዳ ዋና ከተማ ኦታዋ በነበራቸው ቆይታ ነው።
''ካናዳ እና አሜሪካ ከአጋሮቻቸው ጋር በጋራ በመሆን የኢራንን የጦር መሳሪያ አቅርቦት ለማጋለጥ፣ ለመግታት እንዲሁም ለመመከት ይሰራሉ'' ሲሉ ተናግረዋል።
ሩሲያ ከሰሞኑ የዩክሬን ሲቪሎች የሚጠቀሙበትን መሰረተ ልማቶች ማጥቃቷን ቀጥላለች። የኤሌክትሪክ እና የውሃ ብሎም መሰል መሰረተ ልማቶች ክረምት መግባት በጀመረበት ወቅት ማጥቃት በመጀመሩ ስጋትን ፈጥሯል።
ምዕራባዊያኑ እንደሚሉት ኢራን ያመረተቻቸውን ሰው አልባ አውሮፕላኖች ለሞስኮ እያቀረበች ሲሆን የኢራን ወታደራዊ ባለሞያዎች ሩሲያ ወራ በያዘቻት ክሬሚያ ለፓይለቶች የቴክኒክ ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ።
ኪዬቭ መሠረተ ልማቷ ላይ ጥቃት ካደረሱ ድሮኖች መካከል የኢራን ስሪት የሆነውን ሻሄ-136 ድሮን መለየቷን ይፋ አድርጋለች። በተለምዶ ''ካሚካዜ'' በመባል የሚታወቁት እነዚህ ድሮኖች ስያሜያቸውን በሁለተኛው የአለም ጦርነት ወቅት አጥፍቶ በመጥፋት ከሚታወቁት የጃፓን ተዋጊ ጀቶች አግኝተዋል። ድሮኖቹ ጥቃት ካደረሱ በኋላ የሚወድሙ ናቸው።
ዩክሬን ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ሩስያ 400 ድሮኖችን መጠቀሟን ይፋ አድርጋለች።
ባሳለፍነው ረቡዕ የኢራን የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሁሴን አሚር አብዱልሃሚን ክሶቹን ''መሰረተ ቢስ'' ሲሉ አጣጥለውታል። ዩክሬን ለክሷ ማስረጃ እንድታቀርብም ጥይቀዋል።
''ሩስያ የኢራንን ድሮኖች በዚህ ጦርነት መጠቀሟ ከተረጋገጠ በዚህ ጉዳይ በርግጥም ገለልተኛ አይደለንም ማለት ነው'' ሲሉም አክለዋል።