የክልሎች ልዩ ኃይል ህልውና ማብቃቱን የጦር ኃይሎች ኤታማዦር ሹም ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, ena
በአገሪቱ ውስጥ የክልል ልዩ ኃይል የሚባል የፀጥታ አደረጃጀት ከዚህ በኋላ የሌለ መሆኑን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ መናገራቸው ተዘገበ።
ኤታማዦር ሹሙ ይህንን ያሉት የክልል ልዩ ኃይሎችን በመከላከያ፣ በፌዴራል እና በክልል የፀጥታ ተቋማት ውስጥ ለማካተት በተያዘው ዕቅድ እና የተከናወነ ሥራን በተመለከተ በተደረገ ግምገማ ላይ መሆኑን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
በዚህም አዲሶቹን ጨምሮ በክልሎች ከፖሊስ በተለየ ሁኔታ በሥልጠና፣ በትጥቅ እና በአደረጃጀት የተዋቀሩት ልዩ ኃይሎች ከአስር ዓመታት በኋላ ህልውናቸው ያበቃል ማለት ነው።
ሕጋዊነቱ እና አደረጃጀቱ በተመለከተ ለረጅም ጊዜ ጥያቄ ሲነሳባቸው የነበሩት የክልሎች ልዩ ኃይሎች እንዲፈርሱ እና በመደበኛ ፖሊስ እንዲተኩ ሃሳብ ሲቀርብ ቆይቷል።
ባለፉት ጥቂት ሳምንታትም የፌደራል መንግሥት ልዩ ኃይሎችን መልሶ ለማደራጀት ያለውን ዕቅድ ይፋ ካደረገ በኋላ በአማራ ክልል ውስጥ ልዩ ኃይሉን ለማፈረስ ያፈርሳል በሚል ለቀናት ሕዝባዊ ተቃውሞዎች ተካሂደዋል።
በአንዳንድ የአማራ አካባቢዎችም በመከላከያ ሠራዊት እና በተቃዋሚዎች፣ በልዩ ኃይል እና በፋኖ አባላት መካከል በተከሰተ ግጭት የሰው ሕይወት እስከመጥፋት ደርሷል።
ከአማራ ክልል ውጪ አብዛኞቹ የአገሪቱ ክልሎች ለዓመታት ያደራጁትን የታጠቀ ልዩ ኃይል ከፌደራል እና ከክልል የፀጥታ ኃይሎች ጋር ለማዋሃድ መዘጋጀታቸውን እና ተግባራዊ ማድረግ መጀመራቸውን አስታውቀዋል።
የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የመከላከያ ጄኔራሎች፣ ፌዴራል ፖሊስ እና የክልሎች ባለሥልጣናት በተገኙበት ልዩ ኃይሎችን መልሶ በማዋቀር ዙሪያ ግምገማ አድርገዋል።
የክልል ልዩ ኃይሎች የተዋቀሩበት መንገድ ሕጋዊነት ላይ ጥቃቄ ሲነሳበት የቆየ ሲሆን፣ በክልሎች መካከል የተፈጠረው ስጋት እንዲሁም የሚከሰቱ ችግሮችን በኃይል ለመፍታት የሚደረገው እንቅስቃሴ የታጠቀውን የክልሎች ልዩ ኃይል ወደ ፌደራል እና ክልል የፀጥታ ኃይል ውስጥ በማካተት መልሶ ለማዋቀር ምክንያት መሆኑን ኤታማዦር ሹሙ ገልጸዋል።
ስለዚህም “ከዛሬ ጀምሮ የክልል ልዩ ኃይል የሚባል አደረጃጀት እና መዋቅር የለም” በማለት የክልሎች ልዩ ኃይሎች ህልውና ማብቃቱን ገልጸዋል።
በዚህም ምክንያት በአገሪቱ ክልሎች ውስጥ የፀጥታ ሥራዎችን የሚያከናውኑት መከላከያ፣ ፌዴራል ፖሊስ እና የክልል ፖሊሶች ብቻ ይሆናሉ። ከዚህ በኋላም በክልል ልዩ ኃይል ስም “ተልዕኮም ሆነ ግዳጅ የሚቀበል ኃይል አይኖርም” ሲሉ ኤታማዦር ሹሙ መናጋረቸው ተዘግቧል።
ፊልድ ማርሻል ብርሁኑ ጁላ የክልል ልዩ ኃይሎችን ወደ መከላከያ እና ወደ ተለያዩ የፖሊስ ኃይሎች የማካተቱ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን በማመልከት፣ የልዩ ኃይል አባላት በተመደቡበት ዘርፍ በኩል ሥልጠና አግኝተው ሕብረ ብሔራዊ ጠንካራ የፀጥታ ተቋም እንደሚገነባ ገልጸዋል።
በፌደራል መንግሥቱ በቀረበው ዕቅድ መሠረት የክልል ልዩ ኃይል አባላት በምርጫቸው መሠረት ወደ መከላከያ ሠራዊት፣ ፌደራል ፖሊስ እና ክልል ፖሊስ የሚገቡ ሲሆን፣ ፍላጎት የሌላቸውም መቋቋሚያ አግኝተው ወደ ሚመርጡት ሰላማዊ ሕይወት ይመለሳሉ ተብሏል።
የልዩ ኃይል አደረጃጀት ጅማሬ
በኢትዮጵያ የክልል ልዩ ኃይልን ማደራጀት የተጀመረው በ1998 ዓ.ም. በሶማሌ ክልል ውስት የነበረውን የሸማቂ ኃይል እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ነበር።
በወቅቱ በሶማሌ ክልል ከፍተኛ ተጽዕኖ የነበረው የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻ አውጪ ግንባርን (ኦብነግ) ተዋጊዎች ለመቆጣጠር በፌደራል መንግሥቱ ድጋፍ ነበር ልዩ ኃይሉ የተደራጀው።
ቀጥሎ ደግሞ ኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች የራሳቸውን ልዩ ኃይል ማደራጀት ጀመሩ። በዚህም አዲስ የተመሠረቱትን ጨምሮ በሌሎችም ክልሎች ልዩ ኃይል የማቋቋም ልምዱ ተስፋፍቶ ቀጠለ።
የክልሎች ልዩ ኃይሎች በመጀመሪያ ላይ ሲመሰረቱ በፖሊስ ስም የነበረ ሲሆን፣ በዚህም ምክንያት “ልዩ ፖሊስ” በመባል ሲጠሩ ቆይተዋል።
ነገር ግን አደረጃጀታቸው፣ ኃላፊነታቸው እና ትጥቃቸው ከፖሊስ የተለየ ከመሆኑም ባሻገር ከመደበኛ ጦር ሠራዊት ጋር የሚስተካከል በመሆኑ ቀስ በቀስም የእነዚህ ታጣቂ የክልል ኃይሎች መጠሪያ ከልዩ ፖሊስነት ወደ ልዩ ኃይልነት ተሸጋገረ።
እነዚህ ልዩ ኃይሎች የታጠቁ አማጺያን እና የወንጀል ቡድኖች ላይ ያነጣጠሩ ዘመቻዎችን ሲያካሂዱ ቆይተዋል።
በተጨማሪም የወሰን ችግር ባለባቸው ክልሎች መካከል በሚፈጠሩ ግጭቶች ውስጥ የክልሎቹ ልዩ ኃይሎች ጥቃት በመፈጸም ሲከሰሱ ቆይተዋል።
በአገሪቱ ክልሎች ውስጥ ተደራጅተው የሚገኙት ልዩ ኃይሎች አወቃቀር እና ትጥቅን በተመለከተ ለበርካታ ዓመታት ጥያቄ ሲነሳበት እና የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድ በተለያዩ ወገኖች ሃሳብ ሲሰነዘር ቆይቷል።
በሁሉም ክልሎች በሚባል ደረጃ ልይ ኃይሎች ከፖሊስ እና ከአካባቢ የፀጥታ ኃይሎች በተለየ ሁኔታ ወታደራዊ ሥልጠና እና ትጥቅ ያላቸው በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ታጣቂዎችን ባለፉት ዓመታት አደራጅተዋል።












