አርሰናል ዴክለን ራይስን በ105 ሚሊዮን ፓውንድ ከዌስት ሃም ለመግዛት ተስማማ

ታትሟል

አርሰናል 105 ሚሊዮን ፓውንድ በሚጠጋ ዋጋ የዌስት ሃሙን እንግሊዛዊ አማካይ ዴክለን ራይስን ለማስፈረም ተስማምቷል።

ሁለቱ የለንደን ከተማ ክለቦች የ24 ዓመቱ አማካይ ሽያጭ እና ግዥ እንዴት መጠናቀቅ አለበት በሚለው ጉዳይ ላይ ውይይት ተቀምጠዋል።

አርሰናል በያዝነው የክረምት የዝውውር መስኮት ለዴክለን ራይስ ሁለት ጊዜ ጨረታ አቅርቦ በዌስት ሃም ውድቅ ተደርጎበት ነበር።

ዌስት ሃም ለተጫዋቹ የሚፈልገው ገንዘብ 100 ሚሊዮን ፓውንድ ሲሆን፣ አርሰናል በስተመጨረሻ ይህን ገንዘብ ለማቅረብ ተስማምቷል።

የሦስትዮሽ ዋንጫ ባለቤቱ ማንቸስተር ሲቲ ተጫዋቹን በ90 ሚሊዮን ፓውንድ ልግዛው የሚል ጥያቄ ቢያቀርብም በዌስት ሃም ውድቅ ሆኖበታል።

የዌስትሃሙ አምበል ዴክለን ራይስ የክለቡን አካዳሚ ከቼልሲ የተቀላቀለው በፈረንጆቹ 2014 ነበር።

ባለንበት ወር መጀመሪያ ከቡድኑ ጋር የአውሮፓ ኮንፈረንስ ሊግ ዋንጫን በማንሳት ክለቡ ከ43 ዓመታት በኋላ ዋንጫ እንዲያነሳ ምክንያት ሆኗል።

ከለንደኑ ክለብ ጋር ያለው ስምምነት ክረምት 2024 ያበቃ ነበር።

አርሰናል ለተጫዋቹ 100 ሚሊዮን ፓውንድ በጥሬው እና በተለያዩ ጥቅማጥቅሞች ደግሞ 5 ሚሊዮን ፓውንድ ለመጨመር ቃል ገብቷል።

በብሪታኒያ እግር ኳስ 100 ሚሊዮን ፓውንድ ለአንድ ተጫዋቾች ሲከፈል ይህ ሁለተኛው ሲሆን የመጀመሪያው በመሆን ክብረ ወሰኑን የያዘው ጃክ ግሪሊሽ ነው።

ሌላኛው እንግሊዛዊ አማካይ ጁድ ቤሊንግሃም በ88.5 ሚሊዮን ፓውንድ ሪያል ማድሪድን ተቀላቅሏል።

ዋናው ዋጋው 88.5 ሚሊዮን ይሁን እንጂ ጥቅማጥቅሞች ሲጨመሩ 115 ሚሊዮን ሊደርስ ይችላል።

በፕሪሚዬር ሊግ ታሪክ ከፍተኛው ገንዘብ የተከፈለው ለአርጀንቲናዊው አማካይ ኤንዞ ፈርናንዴዝ ነው።

ቼልሲ፤ አርጀንቲናዊውን አማካይ ለማስመጣት ለፖርቹጋሉ ቤንፊካ 107 ሚሊዮን ፓውንድ መክፈሉ ይታወሳል።

ዴክለን ራይስ ለዌስት ሃም 245 ጨዋታዎችን አድርጎ 15 ጎሎች አስቆጥሯል።

ለእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ደግሞ 43 ጊዜ ሲጫወት፣ ባለፈው የዓለም ዋንጫ በአምስቱም ጨዋታዎች ተሰልፎ ነበር።

ባለፈው ዓመት በፕሪሚዬር ሊጉ ማንቸስተር ሲቲን ተከትለው የጨረሱት አርሰናሎች ካይ ሃቨርትዝን ከቼልሲ በ65 ሚሊዮን ፓውንድ አስመጥተዋል።