በቱርክ የድንጋይ ከሰል ማውጫ ላይ በተከሰተ ፍንዳታ 40 ሰዎች ሲሞቱ፣ 11 ቆሰሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሰሜናዊ ቱርክ ውስጥ በሚገኝ አንድ የድንጋይ ከሰል ማውጫ ላይ በተከሰተ ፍንዳታ 40 ሰዎች መሞታቸውን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ አስታወቁ።
የቱርክ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሱሌይማን ሶይሉ እንዳሉት ከአደጋው ስፍራ 58 ሰዎችን በሕይወት ማትረፍ ሲቻል፣ 11 ደግሞ የመቁሰል አደጋ ሲደርስባቸው አንድ ሰው የደረሰበት አልታወቀም።
በጥቁር ባሕር ዳርቻ በምትገኘው አምሳራ በምትባለው ስፍራ አርብ ዕለት በድንጋይ ከሰል ማውጫ ላይ ፍንዳታው ሲከሰት 110 ሰዎች በስፍራው ነበሩ።
ሁሉም ቢያንስ ከምድር በታች 300 ሜትር ወርደው እየሠሩ ነበር።
በፍንዳታው ከመሬት በታች የተቀበሩ ሰዎችን ከዋሻው ለማውጣት የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ሌሊቱን ሙሉ ቁፋሮ ሲያካሂዱ ነበር ያደሩት።
የድንጋይ ከሰል አውጭ ሠራተኞች በጥቁር ጭስ ተሸፍነው እና ዐይናቸው ቀልቶ ወደ ሕክምና መስጫ ሲወሰዱ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምሥል ወጥቷል።
የሠራተኞቹ ቤተሰቦች እና ወዳጆች ሠራተኞቹ ከዋሻው እስከሚወጡ በቦታው ሲጠባበቁም ታይቷል።
የአገር ውስጥ ሚኒስትሩ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፣ በተካሄደው ፍለጋ 40 አስከሬኖች የተገኙ ሲሆን 58 ሠራተኞች በራሳቸው እና በነፍስ አድን ሠራተኞች ከማዕድን ጉድጓዱ ወጥተዋል፤ በዚህም “ግዙፉ የነፍስ አድን ሥራ ወደ መጠናቀቁ ተቃርቧል” ብለዋል።
ፍንዳታው ከመሬት 300 ሜትር ጥልቀት ላይ እንደተከሰተ ይታመናል።
እስካሁን የፍንዳታው መንስኤ ምን እንደሆነ ባይታወቅም፣ የቱርክ ዐቃቤ ሕግ ቢሮ ምርመራ ጀምሯል።
የቱርክ የኢነርጂ ሚኒስትር እንዳሉት፣ በድንጋይ ከሰል ማውጫ ውስጥ ተቀጣጣይ ኬሚካል በመፍጠር በሚታወቀው ፋየርዳምፕ ሳቢያ ፍንዳታው ተከስቶ ሊሆን ይችላል።
ፍንዳታው የተከሰው አንድ ጊዜ እንደሆነም ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን አደጋው የተከሰተበት ባርቲን ግዛትን ዛሬ ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የአማስራ ግዛት ከንቲባ ሬሳይ ካኪር፣ ከፍንዳታው የተረፉ ሰዎች ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ገልጸዋል።
አንድ ከፍንዳታው የተረፈ ሠራተኛ “ጭስ እና አቧራ አካባቢውን ሞልቶት ነበር። ምን እንደተከሰተ አልገባንም” ብሏል።
የድንጋይ ከሰል ማውጫው በቱርክ መንግሥት የሚተዳደር ነው።
በአገሪቱ የከፋ የድንጋይ ከሰል ማውጫ ቦታ አደጋ የተከሰተው እአአ በ2014 ሲሆን 301 ሰዎች ሞተዋል።












