በአዲስ አበባ ባለፉት 6 ወራት 15 የእሳት ቃጠሎዎች ሆነ ተብሎ መፈጸማቸው ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Federal Police
በስድስት ወራት ከደረሱት የእሳት ቃጠሎዎች 16 ያህሉ ሆን ተብለው የተፈጸሙ መሆናቸውን እና ከእነዚህም መካከል 15ቱ በአዲስ አበባ መከሰታቸውን የፌደራል ፖሊስ በፎረንሲክ ምርመራ ማረጋገጡን አስታወቀ።
በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ በመላው አገሪቱ ከደረሱት የእሳት አደጋዎች መካከል 90 በመቶ በላይ የሚሆኑት የደረሱት በዋና ከተማዋ ውስጥ እንደሆነ ፖሊስ ተገልጿል።
በ2016 የበጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ውስጥ በአገር አቀፍ ደረጃ 139 የእሳት ቃጠሎዎች መድረሳቸውን የፌዴራል ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጄይላን አብዲ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከእነዚህ የእሳት አደጋዎች ውስጥ 130 ያህሉ የተከሰቱት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ መሆኑን ኃላፊው አመልክተው፣ ቀሪዎቹ ዘጠኝ ቃጠሎዎች የተከሰቱት በአፋር፣ በደቡብ ኢትዮጵያ እና በሐረሪ ክልሎች መሆኑንም አክለዋል።
የፌደራል ፖሊስ የእሳት ቃጠሎዎቹን መንስኤ ለማወቅ የፎረንሲክ ምርመራ ማድረጉን የሚገልጹት አቶ ጄይላን፤ በተደረገው ምርመራ ከስምንቱ ውጪ የሌሎቹ ቃጠሎዎች ምክንያት መለየቱን አስረድተዋል። ባለፉት ስድስት ወራት ለተከሰቱ የእሳት ቃጠሎዎች በቀዳሚነት የተጠቀሰው ምክንያት በኤሌክትሪክ የቴክኒክ ችግር መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በዚህ ምክንያት የደረሱ የእሳት አደጋዎች ብዛት 76 መሆናቸውን የተናገሩት አቶ ጄይላን፤ ይህ ቁጥር ከአምናው ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻጸር ተመሳሳይ መሆኑን ገልጸዋል። ለ24 የእሳት አደጋዎች መነሻ በመሆን በሁለተኛነት የተቀመጠው ጉዳይ በተለያዩ ምክንያቶች የሚፈጠር የመካኒካል ችግር እንደሆነ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አንስተዋል።
የፌደራል ፖሊስ የፎረንሲክ ምርመራ እንደሚያመለክተው ሆን ብሎ የእሳት ቃጠሎ እንዲከሰት ማድረግ በስድስቱ ወራት ውስጥ ለተከሰቱት ቃጠሎዎች ሌላ ምክንያት ነው። በዚህ መልኩ በአዲስ አበባ ከተማ 15 እና በአፋር ክልል ደግሞ አንድ የእሳት ቃጠሎዎች ሆን ተብለው መከሰታቸውን አቶ ጄይላን ጠቅሰዋል።
ግለሰቦች የኢንሹራንስ ካሳ ለማግኘት፣ የራስን ጥቅም ለማስጠበቅ ወይም ሌላ ሰው ላይ ጉዳት ለማድረስ ሲሉ ሆነ ብለው የእሳት ቃጠሎ እንደሚያስነሱ እንደተሰደረበትም ገልጸዋል።
አቶ ጄይላን፤ “ኢንሹራንስ ለማግኘት ያረጀ ወይም አልሸጥ ያለ መኪና አቃጥለው ‘በእሳት አደጋ ነው’ ብለው ኢንሹራንስ [ጉዳቱን] እንዲሸፍንላቸው የሚፈልጉ አሉ” ሲሉ አንዱን ምክንያት ለቢቢሲ ጠቅሰዋል።
ይህ ዓይነቱ ቃጠሎ በብዛት በተሽከርካሪዎች ላይ እንደሚደርስ እና ቤቶችም እንደሚገኙበት አንስተዋል። ሆነ ብሎ የእሳት ቃጠሎ ከማስነሳት ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር የዋሉ ሰዎች መኖራቸውን የጠቀሱት አቶ ጄይላን፤ ምን ያህል ሰዎች እንደተያዙ እና የደረሰውን አደጋ መጠን ከመግለጽ ተቆጥበዋል።
የፌዴራል ፖሊስ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው እንደሚያስረዱት በስድስት ወራቱ ውስጥ በዚህ ዓይነቱ ምክንያት የደረሱት የእሳት አደጋዎች ብዛት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻጸር በስድስት ቀንሷል።
በአጠቃላይ ከደረሱት የእሳት ቃጠሎዎች መካከል 15 ያህሉ በቸልተኝነት እና በጥንቃቄ ጉድለት ምክንያት የተከሰቱ መሆናቸውን አቶ ጄይላን ተናግረዋል።
በስድስት ወራት ውስጥ በተከሰቱት የእሳት ቃጠሎዎች ምክንያት በሰው ላይ ስለደረሰው ጉዳት እና በንብረት ላይ የደረሰውን የውድመት መጠንን በተመለከተ የተሰጠ አሃዝ የለም።












