ከአሜሪካ እስር ቤት የተፈታው ሩሲያዊው ‘የሞት ነጋዴ’ አክራሪ የፖለቲካ ፓርቲን ተቀላቀለ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ከቀናት በፊት ከአሜሪካ እስር ቤት የተፈታውና በቅጽል ስሙ “የሞት ነጋዴ” የሚባለው ሩሲያዊ ቪክተር ቡት የፖለቲካ ፓርቲን ተቀላቀለ።
ቪክተር ቡት የተቀላቀለው ፓርቲ ክሬምሊንን የሚደግፍ የአክራሪ ብሔርተኞችን ፓርቲ ነው።
ቪክተር ቡት ከቀናት በፊት ከአሜሪካ እስር ቤት ሊፈታ የቻለው ሩሲያ በእስር ላይ ለነበረችው ዝነኛዋ አሜሪካዊት የቅርጫት ኳስ ተጫዋች ብሪትኒ ግራይነር ልዋጭ ይህ ዜጋዬ ይፈታልኝ በማለቷ ነው።
የቪክተር ቡትን እና የብሪትኒ ግራይነርን የእስረኞች ልውውጥ ያሳለጡት የሳኡዲው ልዑል መሐመድ ቢን ሰልማንና የተባበሩት አረብ ኢምሬቱ አቻቸው ነበሩ።
ዝነኛዋ አሜሪካዊት የቅርጫት ኳስ ተጫዋች ብሪትኒ ግራይነር በሩሲያ ለእስር የተዳረገችው የካናቢስ ዘይት ሻንጣዋ ውስጥ በመገኘቱ ነበር።
‘የሞት ነጋዴ’ የሚል ቅጽል የተሰጠውና ሆሊውድ ከሕይወት ታሪኩ በጨለፈው ምናባዊ ፈጠራ ፊልም እስከመሥራት የተደረሰለት ሩሲያዊው ቪክተር ቡት የጦር መሣሪያ የሲራራ ነጋዴ ነበር።
በተለይም ጨቋኝና ጨፍላቂ ለነበሩ የአፍሪቃና እሲያ አምባገነኖች፣ አንዲሁም በሦስተኛው ዓለም ላሉ አማጺ ቡድኖች በምሥጢር የጦር መሣሪያ ሲያቀርብ ነው የሕይወቱን ሲሶ ያሳለፈው።
አሜሪካ ይህንን የ55 ዓመት ግለሰብ ስታድነው ኖራ ከቆየች በኋላ ከ10 ዓመት በፊት ታይላንድ ዋና መዲና ባንኮክ ካረፈበት ሆቴል በቁጥጥር ሥር እንዲውል አድርጋለች።
ከወራት በኋላም ተላልፎ ተሰጥቷት 25 ዓመት ጽኑ ፍርድ አጽንታበት ነበር።
አሁን ቡት አባል ሆኖ የተመዘገበበት የፖለቲካ ፓርቲ ኤልዲፒአር የሚባል ነው።
ይህ ፓርቲ አክራሪ የሩሲያ ብሔርተኞች የሚገኙበት ሲሆን የክሬምሊን ቀኝ እጅ በመሆን የሚታወቅ ነው።
“በሩሲያ ምርጡ የፖለቲካ ፓርቲ አባል በመሆኔ ላቅ ያለ ደስታ ይሰማኛል’ ብሏል ቪክተር ቡት።
የዚህ ፓርቲ መሪ የሆኑት ሚስተር ስለትስኪ ባደረጉት ንግግር ደግሞ፥ ‘እያንዳንዱን ሩሲያዊ እስረኛ ለእናት አገሩ እናበቃዋለን’ ሲሉ ዝተዋል።
ይህ ቡት አባል የሆነበት ፓርቲ የተመሠረተው በ1990ዎቹ ሲሆን መሥራቹ ደግሞ ዝነኛው ፖለቲከኛ ቭላድሚር ዚሪኖቭስኪ ነበር።
ዚሪኖቪስኪ ይበልጥ የሚታወቀው ሩሲያ ኒውክሌር ጦር መሣሪያዋን ጥቅም ላይ ማዋል አለባት በሚል አወዛጋቢ አቋም ነበር።
ቪክተር ቡት ለጊዜው በፓርቲው ለአመራርነት ምርጫ እንደማይወዳድር ይፋ አድርጓል።
ይህ የአክራሪ ብሔርተኞች ፓርቲ ሩሲያ ዩክሬንን ሙሉ በሙሉ መጠቅለል አለባት ብሎ ያምናል።












