የቴስላ መኪና ላይ ያነጣጠረ ጉዳት ያደረሱ እስከ 20 ዓመት እስር ይጠብቃቸዋል- የአሜሪካ ጠቅላይ አቃቤ ህግ

ጉዳት የደረሰበት ቴስላ መኪና

የፎቶው ባለመብት, US Justice Department

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በኤሎን መስክ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ኩባንያ የሚመረተው ቴስላ መኪናን ላይ ያነጣጠረ ጉዳት አድርሰዋል የተባሉ ሶስት ተከሳሾች እስከ 20 ዓመት እስር እንደሚጠብቃቸው የአሜሪካ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ጄነራል ፓም ቦንዲ ተናገሩ።

በቴስላ መኪናዎች፣ አከፋፋዮች እና ቻርጅ ማረጊያ ጣቢያዎች ላይ ሆን ብለው የሚደርሱ ጉዳቶች "በአገር ውስጥ ሽብርተኝነት" እንደሚፈረጁ ጠቅላይ አቃቤ ህጓ አክለዋል።

ሶስቱ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን እንዲሁም ክሳቸውን በተመለከተ ቀደም ሲል አቃቤ ህግ አስታውቆ ነበር።

ቱጃሩ ኤለን መስክ በትራምፕ አስተዳደር ላይ እያሳደረ ለመጣው የጎላ ተፅእኖ ምላሽ ፤በመላው አገሪቱ የሚገኙ የቴስላ አከፋፋዮች የአደባባይ ተቃውሞው ኢላማ ሆነዋል።

በተጨማሪም መኪኖቹ ላይ ያነጣጠረ ውድመት እና የእሳት ቃጠሎዎች ጥቃቶችም ደርሶባቸዋል።

በአሜሪካ የአገር ውስጥ ሽብርተኝነትን የሚመለከተ የተለየ ህግ የለም። ነገር ግን የተፈረደባቸው ወንጀለኞች ከሽብርተኝነት ጋር ግንኙነት ካላቸው አቃብያነ ህግ ረዘም ያለ እስር መጠየቅ ይችላሉ

ትራምፕ እና መስክ ጥቃቶቹን የአገር ውስጥ ሽብርተኝነት ሲሉ ጠርተውታል።

የፍትህ ዲፓርትመንት ሐሙስ ዕለት ባወጣው መግለጫ የቴስላ መኪኖች ላይ ጉዳት አድርሰዋል ተብለው የተጠረጠሩ ሰዎችን ስም አልጠቀሰም።

ሆኖም በመግለጫው ላይ የተገለጹት የሶስቱ ሰዎች እስራት እንዲሁም የክሱ ዝርዝር ቀደም ሲል አቃቤ ህግ ይፋ ካደረገው የግለሰቦቹ ክሶች ጋር ተመሳሳይ ነው።

ከተጠርጣሪዎቹ መካከል በኮሎራዶ የቴስላ መኪና መሸጫ አጠገብ ከታየች በኋላ በአውዳሚ መሳሪያና ተንኮል የተሞላበት ንብረት ማውደም የተከሰሰችው የ42 ዓመቷ ሉሲ ኔልሰን ትገኝበታለች።

የመኪና አከፋፋዩ ጥቃት የደረሰበት ሞሎቶቭ ኮክቴል በተሰኘው ተቀጣጣይ ፈንጂ መሳይ እንዲሁም በግራፊቲ ጽሁፎች ሲሆን ይህም ከ5 ሺህ -20 ሺህ ዶላር የሚደርስ ጉዳት እንዳስከተለም ለፍርድ ቤቱ የቀረበው የከሳሹ ክስ ያስረዳል።

ተጠርጣሪዋ ጥፋተኛ አይደለሁም ብላለች።

በኦሪጎን በሚገኘው የቴስላ መከፋፈያ በኋላ ተቀጣጣይ ፈንጂ መሳይ መጣሉን ተከትሎ የ41 ዓመቱ አደም ማቲው አውዳሚ መሳሪያ በመያዝ ተከሷል።

የግለሰቡ የመጀመሪያ ደረጃ የችሎት ሂደት በሚያዝያ ወር እንደሚጀመርም ይጠበቃል።

ሶስተኛው ተከሳሽ በደቡብ ካሮላይና ግዛት በቴስላ መኪና ላይ ተቀጣጣይ ፈንጂ የሆነውን ሞሎቶቭ ኮክቴል በመወርወር እንዲሁም በመኪናው ላይ ቀለም በመርጨት ክስ የተመሰረተበት የ24 ዓመቱ ዳንኤል ክላርክ ፓውንደር ነው።

"ያለ ምንም መዘዝ ወንጀል የሚፈጸምበት ጊዜ አክትሟል" ሲሉ ቦንዲ ተናግረዋል።

"በቴስላ ንብረቶች ላይ የተቃጣውን ይህንን የአገር ውስጥ የሽብር ማዕበል ከተቀላቀሉ የፍትህ መስሪያ ቤት ወደ እስር ቤት እንደሚወስድዎት ማስጠንቀቂያ ይሁን" ሲሉም አስጠንቅቀዋል።