እስራኤል በጋዛ መኖርያ ሕንጻ ላይ በፈጸመችው ጥቃት 29 ሰዎች መገደላቸውን የሕክምና ባለሙያዎች ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
እስራኤል በምሥራቅ ጋዛ በመኖርያ ሕንጻ ላይ በፈጸመችው ጥቃት ሕጻናትን ጨምሮ 29 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን በአካባቢው የሚገኝ ሆስፒታል ገለፀ።
በሃማስ የሚመራው የሲቪል መከላከያ ኤጀንሲ በበኩሉ ማክሰኞ ማለዳ የጦር አውሮፕላኖች ሼጃያ በሚባል ስፍራ በሚገኘው አል ሃዋሺ መስኪድ አቅራቢያ የሚገኙ ቦታዎችን ዒላማ አድርገዋል ብሏል።
በእስራኤል የአየር ጥቃት መጀመሪያ ላይ 23 ሰዎች መገደላቸው የተገለፀ ቢሆንም፣ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ሌሎች በርካታ ሰዎችን ከፍርስራሹ ውስጥ ሟቾችን ለማውጣት ፍለጋ ላይ በመሆናቸው ቁጥሩ ሊጨምር እንደሚችል ተነግሯል።
ረቡዕ ምሽት አጠቃላይ የሟቾች ቁጥር በይፋ ሳይገለፅ፣15 አስከሬኖች መገኘታቸው ብቻ ይፋ ሆኗል።
የእስራኤል ጦር በአካባቢው ጥቃቶችን በማቀድ እና በማስፈፀም ኃላፊነት ያለውን "ከፍተኛ የሃማስ አሸባሪ" መትቻለሁ ብሏል።
በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከል "ዒላማቸውን ለይተው የሚመቱ የጦር መሳሪያዎችን" ከመጠቀም ጀምሮ በርካታ እርምጃዎች ተወስደዋል ሲልም ገልጿል።
ወታደራዊ ቡድኑ፣ሃማስ ሆን ብሎ ሰላማዊ ሰዎችን እንደ ጋሻ ይጠቀማል በማለት ሀማስን በዓለም አቀፍ ሕግ ጥሰት ከስሷል።
ከሸጃያ የተገኘ ተንቀሳቃሽ ምስል፤ በጭንቀት የተዋጡ ቤተሰቦች እና የነፍስ አድን ሠራተኞች በአቧራ የተሸፈኑ የትንንሽ ሕጻናት አስከሬኖችን ከፍርስራሹ ውስጥ አውጥተው ሲወሰዱ ያሳያል።
የ26 ዓመቱ አዩብ ሳሊም ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል እንደተናገረው ማክሰኞ ጠዋት የአየር ድብደባ የተፈጸመበት የመኖሪያ ሕንጻ አካባቢ፤ "በድንኳኖች፣ በተፈናቀሉ ሰዎች እና በመኖሪያ ቤቶች" የተጨናነቀ ነው።
ሕንጻው "በበርካታ ሚሳኤሎች" መመታቱን ጠቅሶ፣ " ፍንጥርጣሪዎች በሁሉም አቅጣጫ ይበሩ ነበር" ብሏል።
"አቧራ እና ፍርስራስ አካባቢውን ሞላው፤ ምንም ነገር ማየት አልቻልንም፤ የሕዝቡ ጩኸት እና ድንጋጤ ብቻ ነበር" ሲል አክሏል።
"በእውነቱ አሰቃቂ እልቂት ነው።"
ሃማስ በበኩሉ የእስራኤል ጦር "ሰቅጣጭ ጭፍጨፋ ፈጽሟል" ብሏል።
በሺዎች የሚቆጠሩ የሼጃያ ነዋሪዎች ባለፈው ሳምንት የእስራኤል ጦር "የአሸባሪ መሰረተ ልማቶችን" ለማፍረስ እየሰራሁ በመሆኑ ከአካባቢውን ውጡ ካለ በኋላ ለቅቀው መውጣታቸውን ይናገራሉ።
ነገር ግን ነዋሪዎቹ ረቡዕ ዕለት ጥቃት የደረሰበት ስፍራ፣ ለቅቀው እንዲሄዱ ትእዛዝ ያልተሰጠበት በመሆኑ ብዙ ቤተሰቦች እዚያው መቅረታቸውን ተናግረዋል።
በሼጃያ የሚኖሩ አንድ አዛውንት "ይህ ለተፈናቃዮች አስተማማኝ ቦታ እንደሆነ ተነግሮናል፤ በተቃራኒው መኖሪያ ቤቶችን እያነጣጠሩ በሚሳኤል ይደበድባሉ። ልጆቹ ምን አደረጉ? በእስራኤል ጦር ላይ ሮኬቶችን ይተኩሳሉ?" ሲሉ ለቢቢሲ አረብኛ ጋዛ ላይፍላይን ፕሮግራም ተናግረዋል።
በሃማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር ማክሰኞ ዕለት እስራኤል በጋዛ በፈጸመችው ጥቃት ባለፉት 24 ሰዓታት ቢያንስ 33 ሰዎች መገደላቸውን አስታውቆ ነበር።
ይህም እስራኤል ዳግም በጋዛ የምትፈጽመውን ጥቃት አጠናክራ ከቀጠለች በኋላ የተገደሉትን ፍልስጤማውያን ቁጥር 1,482 አድርሶታል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የእስራኤል ጦር ባለፉት ቀናት በጋዛ 45 "የሽብርተኛ ዒላማዎችን"፣ የመሳርያ ማምረቻዎችን እና ሮኬት ማስወንጨፊያዎችን ጨምሮ መደብደቡን ተናግሯል።
አክሎም የእግረኛ ጦሩ በደቡብ ጋዛ ሼጃያ ወደሚባል አካባቢ እና "ሞራግ ኮሪዶር" በመባል ወደሚታወቅ ስፍራ እየተጠጋ መሆኑን ገልጿል።
ወታደራዊ ኮሪደሩ፣ በራፋህ ነዋሪዎች እንዲወጡ የተደረገባቸው አካባቢዎች እና በአጎራባች ካን ዮኒስ መካከል ያለውን ስፍራ ይዞ የተመሰረተ ነው።
የእስራኤሉ የመከላከያ ሚኒስትር፣ እስራኤል ካትዝ ረቡዕ ዕለት አካባቢውን የጎበኙ ሲሆን "እኛ አሁን ሰርጡን ከፋፍለን ደረጃ በደረጃ ጫናችንን እየጨመርን ነው፣ ስለዚህም እነሱ [ሃማስ] ታጋቾቻችንን ይሰጡናል" ብለዋል።
"ከራፋህ ሙሉ በሙሉ ነዋሪዎች ለቅቀው አካባቢው የደህንነት ቦታ ይሆናል፤ አሁን እያደረግን ያለነው ይህንን ነው" ሲሉም አክለዋል።
ባለፉት ሦስት ሳምንታት ውስጥ ተጨማሪ 390,000 ሰዎች ተፈናቅለዋል።
ከግዛቱ ውስጥ ሁለት ሦስተኛው አሁን በእስራኤል ጦር "የማይደረስበት" ስፍራ ተብሎ የተለየ ወይም የልቀቁ ትእዛዝ የተሰጠበት መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ይናገራል።
ሐማስ መስከረም መጨረሻ ላይ በፈጸመው ጥቃት 1,200 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ 253 ሰዎች ታግተው መወሰዳቸው ይታወሳል።
እስራኤል በጋዛ ውስጥ በፈጸመችው ጥቃት ከ50 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ከጋዛ የጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።
ከእነዚህም ውስጥ አብዛኛዎቹ ሴቶች እና ሕፃናት መሆናቸውንም በሐማስ አስተዳደር ሥር ካለው የጤና ሚኒስቴር የወጣው መረጃ አመልክቷል።
እስራኤል በጋዛ በፈጸመችው የተቀናጀ እና የማያባራ ጥቃት ሁለት ሦስተኛው የጋዛ ሕንጻዎች መውደማቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል።












