ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ማሸነፍ የናፈቀው ማንቸስተር ሲቲ በቶተንሀም 4-0 ሲሸነፍ መድፈኞቹ ድል ቀንቷቸዋል
ማንቸስተር ሲቲ ለአምስተኛ ተከታታይ ጊዜ ሽንፈት ቀምሷል። ቅዳሜ ምሽት በነበረው ፍልሚያ በሜዳው በቶተንሀም 4 ለምንም ተረትቷል።
ጄምስ ማዲሰን ሁለት ጊዜ ሲያስቆጥር ፔድሮ ፖር እና ብሬናን ጆንሰን በሁለተኛው አጋማሽ ሁለት አክለው ሲቲ በ52 ጨዋታ ለመጀመሪያ ጊዜ በሜዳው ሽንፈት እንዲከናነብ አድርገዋል።
ሲቲ ለመጨረሻ ጊዜ በሜዳው እንዲህ በሰፋ ልዩነት የተሸነፈው በአውሮፓውያኑ 2003 ሲሆን በወቅቱ በአርሰናል 5-1 መረታቱ ይታወሳል።
ፔፕ ጉዋርዲዮላ የሲቲ አሰልጣኝ ሆነው ከተሾሙ በኋላ ሲቲ ሶስት ተከታታይ የፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎችን ሲሸነፍ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ፔፕ ባለፈው ሐሙስ ነው ከሲቲ ጋር ያላቸውን ውል በሁለት ዓመታት ያራዘሙት። የቶተንሀም ደጋፊዎች “ነገ ጠዋት ትባረራለህ” እያሉ ሲያዜሙ ተሰምተዋል።
ጉዋርዲዮላ በአሰልጣኝነት ዘመናቸው በሜዳቸው በ4 ጎሎች ልዩነት ተሸንፈው አያውቁም።
ያለሁለት ቋሚ ተከላካዮች ወደ ሲቲ ሜዳ ያቀናው ቶተንሀም ከዚህ ቀደም የነበረውን ጨዋታ በኢፕስዊች በሜዳው ቢሸንፈም ከዚህ አገግሞ ያለፈውን የውድድር ዘመን ባለድል ሲቲ ረምርሞ ተመልሷል።
አማካዩ ሮድሪ በጉዳት ምክንያት ረዘም ላለ ጊዜ አይሰለፍም። የባለን ደ ኦር አሸናፊው ሮድሪ ከጨዋታው በፊት ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል። ሮድሪ ሽልማቱን ይዞ ሜዳው መሐል ሲጨፍር ታይቷል።
ነገር ግን የሲቲ ደጋፊዎች የደስታ ሙዚቃ ወደ ሐዘን የተቀየረው በግማሽ ሰዓት ውስጥ ነው። ቶተንሀም በመጀመሪያው አጋማሽ 2 ጎል በማስቆጠር የበላይነቱን ይዞ ነው ወደ መልበሻ ክፍል የገባው።
ሲቲ በደረጃ ሰንጠረዡ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። የሊጉ መሪ ሊቨርፑል እሑድ ከሳውዝአምፕተን ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ ካሸነፈ የነጥብ ልዩነቱን 8 ማድረስ ይችላል።
ቶተንሀም ወደ ስድስተኛ ደረጃ ከፍ ያለ ሲሆን ከሲቲ በአራት ነጥብ ዝቅ ብሎ ተቀምጧል።
በሌላ የቅዳሜ ከሰዓት የፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታ አርሰናል በሜዳው ኖቲንግሀም ፎረስትን 3-0 ማሸነፍ ችሏል። የቀኝ ክንፍ መስመር ተጫዋቹ ቡካዮ ሳካ የመጀመሪያውን ጎል ሲያስቆጥር፤ ቶማስ ፓርቴ ሁለተኛውን እንዲሁም ታዳጊው ኢታን ንዋኔሪ ሶስተኛዋን ጎል አስቆጥሯል።
ቼልሲ ከሜዳው ውጭ ሌስተር ሲቲን 2-1፤ ብራይተን ቦርንመዝን በተመሳሳይ 2-1፤ ዎልቭስ ደግሞ ፉልሀምን 4-1 ረትተዋል። አስተን ቪላ ከክሪስታል ፓላስ 2 አቻ፤ ኤቨርተን እና ብሬንትፈርድ ደግሞ ያለምንም ጎል ተለያይተዋል።
እሑድ ከሰዓት በሚደረጉ ጨዋታዎች ሳውዝአምፕተን የሊጉ መሪ ሊቨርፑልን ያስተናግዳል። ኢፕስዊች ደግሞ አዲስ አሰልጣኝ ከቀጠረው ዩናይትድ ይጫወታል።
ፖርቹጋላዊው አዲሱ የማንቸስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ሩበን አሞሪም የመጀመሪያ ጨዋታዎችን የሚያደርጉ ሲሆን ምን ዓይነት አሰላለፍ ይዘው ይገባሉ የሚለው በጉጉት እየተጠበቀ ነው።
ሰኞ ምሽት ኒውካስል ከዌስት ሀም በሴይንት ጄምስ ፓርክ ይጫወታሉ።