እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት የሄዝቦላህ ከፍተኛ አዛዥን ገደለች

መሐመድ ኒማህ ናስር

የፎቶው ባለመብት, Hezbollah

ታትሟል

እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ በፈጸመችው የአየር ጥቃት አንድ ከፍተኛ አዛዥ መገደላቸውን ሄዝቦላህ ገለጸ።

በኢራን የሚደገፈው የታጣቂው ቡድን በእስራኤል የሮኬት ጥቃት በመፈጸም የአጸፋ ምላሽ መስጠቱንም አስታውቋል።

መሐመድ ኒማህ ናስር በእስራኤል ጥቃት የተገደሉት የሄዝቦላህ ከፍተኛ አመራር አባል ናቸው።

ለዘጠኝ ወራት ያህል በዘለቀው የድንበር ዘለል ጥቃት በእስራኤል ከተገደሉ የታጣቂው አንዱ ሲሆኑ ይህ ጥቃት ወደ ሙሉ ጦርነት እንዳይቀየር ስጋት ተፈጥሯል።

ሄዝቦላህ “ለግድያው ምላሽ” በሚል 100 ሮኬቶችን እና ሚሳኤሎችን በእስራኤል ወታደራዊ ዒላማዎች ላይ ማስወንጨፉን ተናግሯል።

ባዶ ስፍራ ላይ የወደቁ በርካታ ሮኬቶች እሳት ከማስነሳት ውጭ ምንም አይነት ጉዳት አላደረሱም ሲል የእስራኤል ጦር አስታውቋል።

ናስር ከደቡብ ምዕራብ ሊባኖስ ሮኬቶችን ለማስወንጨፍ ኃላፊነት ያላቸውን የሄዝቦላህ እዝ አዛዥ እና “በርካታ የሽብር ጥቃቶችን" በመምራት የሚታወቁ ናቸው ሲል ጦሩ አክሏል።

ባለፈው ወር ሄዝቦላህ በአንድ ቀን ከ200 የሚበልጡ ሮኬቶችን እና ሚሳኤሎችን ወደ ሰሜናዊ እስራኤል እንዲያስወነጭፍ ምከንያት ከሆነው እና በእስራኤል ጥቃት ከተገደለው ታሌብ ሳሚ አብዱላህ “ጋር በትብብር ይሠራ ነበር” ሲል ገልጿቸዋል።

ሄዝቦላህ የአጸፋ ምላሽ ሰጥቷል

የፎቶው ባለመብት, EPA

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከዚያ ወዲህ ውጥረቱን ለማርገብ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን ጨምረው ነበር።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና አሜሪካ ኢራን እና ሌሎች ቡድኖችን ሊያሳትፍ ይችላል ተብሎ የተሰጋውን ጦርነት በመጥቀስ አስጠንቅቀዋል።

በእስራኤል እና በሐማስ መካከል በጋዛ ጦርነት ከጀመረበት መስከረም 26 ጀምሮ በእስራኤል-ሊባኖስ ድንበር ላይ በየቀኑ ማለት በሚባል ደረጃ የተኩስ ልውውጦች አሉ።

ሄዝቦላህ በኢራን የሚደገፈውን የፍልስጤም ታጣቂ ቡድን በመደገፍ እየሠራ መሆኑን ተናግሯል።

ሁለቱም ቡድኖች በእስራኤል፣ በእንግሊዝ እና በሌሎች አገራት በአሸባሪነት የተፈረጁ ናቸው።

ዲፕሎማሲው ካልተሳካ በሰሜናዊው ድንበር ላይ ያለውን የጸጥታ ሁኔታ ወደነበረበት ለመመለስ ወታደራዊ ሃይል እንደሚወስዱ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ የእስራኤል ባለስልጣናት ደጋግመው አስጠንቅቀዋል።

“ሄዝቦላህን በየቀኑ ጠንከር አድርገን እየመታነው ነው። በሊባኖስ የሚያስፈለገውን ማንኛውንም እርምጃ ለመውሰድ በሙሉ ዝግጁነት ላይ እንገኛለን። እኛ ስምምነትን እንመርጣለን። እውነታው የሚያስገድደን ከሆነ ግን እንዴት መዋጋት እንዳለብን እናውቃለን” ሲሉ የመከላከያ ሚኒስትሩ ዮአቭ ጋላንት ረቡዕ ዕለት ገልጸዋል።

በታጠቀው መሣሪያ እና ከሐማስ ጋር ጥብቅ ግንኙነት እንዳለው የሚታሰበው ሄዝቦላ ከእስራኤል ጋር ወደ ሙሉ ጦርነት መግባት እንደማይፈልግ እና በጋዛ የተኩስ አቁም እንዲኖር እንደሚፈልግ አስታውቋል።

የቡድኑ ምክትል መሪ ናኢም ቃሴም ማክሰኞ ዕለት ከአሶሼትድ ፕሬስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “እስራኤል የፈለገችውን መወሰን ትችላለች። የእኛ ምላሽ ግን በእስራኤል በተቀመጠው ህጎች ውስጥ እንደማይሆኑ መጠበቅ አለበት” ብለዋል።

እስካሁን በሊባኖስ ከ400 በላይ ሰዎች መገደላቸው የተዘገበ ሲሆን አብዛኞቹ የሄዝቦላህ ተዋጊዎች ናቸው ተብሏል። በእስራኤል በኩል በአብዛኛው ወታደሮች የሆኑ 25 ሰዎች ተገድለዋል።

በሁለቱም አገራት ድንበር አቅራቢያ ይኖሩ የነበሩ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈናቅለዋል።